የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በስልክ መወያየታቸው ተገልጿል።
“በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያሉ የእርስ በርስ ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ የፖለቲካ ውይይት ወሳኝነት አለው” ሲሉ አንቶኒ ብሊንከን ከጠ/ሚኒስትር አብይ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ወቅት መናገራቸው የመስሪያ ቤታቸው መግለጫ አመላክቷል።
አሜሪካ “በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት ያሳስባታል” ሲሉ መናገራቸውን በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በስልክ ያወሩት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ዙሪያ እንደነበር ጸ/ቤታቸው ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አንቶኒ ብሊንከን “ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ለምታደርገው ጥረት ሀገራቸው እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ናት” ሲሉ መናገራቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአፍሪካ ቀንድ እየተካረረ በመጣው ውጥረት ዙሪያም መምከራቸውንም የመስሪያ ቤታቸው ቃል አቀባይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ላይ በህወሃት ታጣቂዎች መመታቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊን ህይወታቸውን ያጡበት ይህ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከሁለት ዓመት በፊት በተፈረመ የሰላም ስምምነት ጦርነቱ ቆሟል፡፡
ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ውድመት ያደረሰው ይህ ጦርነት በሰላም ስምምነት ቢጠናቀቅም በአማራ ክልል አዲስ ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡
የፌደራል መንግስት ክልል የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም አደራጃለሁ በሚል ውሳኔ ካሳለፈበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች አማካኝነት ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣቸው ተከታታይ ሪፖርቶች በአማራ ክልል ንጹሃን ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ እና ምሁራንን ጨምሮ ሰዎች በጅምላ እየታሰሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ከሰኔ ወር ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ጦርነት ከ160 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡
ግድያ ከተፈጸመባቸው ዜጎች መካከል የአዕምሮ ህመምተኞች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡