በኢትዮጵያ ኃይል የበዛበትና በንፁኃን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲቆም አሜሪካ አሳሰበች

በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተመድ ጉባዔ ጎን ለጎን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሞሊ ፊ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ኃይል የበዛበት የመንግሥት ምላሽና ንፁኃን ላይ ያነጣጠረ የታጣቂዎች ጥቃት እንዲቆም አሳስበዋል።

ረዳት ሚኒስትሯ ከሁለት ዓመታት በፊት የተካሄደውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም፣ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን ያለ ማቋረጥ ውትወታ እናደርጋለንም ብለዋል።

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ግጭት በተመለከተ ያለንን ሥጋት በመግለጽ እንዲቆም በግል በሚደረግ ውይይትና በይፋ በሚኖሩ መግለጫዎች እየጠየቁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ታጣቂዎች በንፁኃንና በመንግሥት መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን የገለጹት ሞሊ ፊ የመንግሥት ኃይል የበዛበት ምላሽ ግን ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡

መንግሥታቸው በኢትዮጵያ መንግሥትና በታጠቁ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የንፁኃን ሞት እንዲቆምና በውይይት እንዲፈታ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ካሳለፍነው ሳምንት የአራት ወራ ልዩ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ምርመራ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ጋምቤላ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ከህግ ውጪ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስር፣ እገታ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በንጹሀን ላይ ተፈጽመዋል ብሏል፡፡

ከሰኔ ወር ጀምሮ ባሉት አራት ወራት ውስጥ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ጦርነት ከ160 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

ግድያ ከተፈጸመባቸው ዜጎች መካከል የአዕምሮ ህመምተኞች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

ጎንደር፣ የጎጃም አካባቢዎች፣ ደብረሲና፣ አታዬ፣ ሸዋሮቢት እና ሌሎችም ቦታዎች ያሉ ሲሆን መረጃ ለፋኖ ትሰጣላችሁ፣ የመንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ ናችሁ እና ያለ ምንም ምክንያት ንጹሃን በመኖሪያ ቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያናት እና በጉዞ ለይ እያሉ እንደተገደሉም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል ይገኙበታል።

ኢሰመኮ አስገድዶ መሰወረንና ሰዎች ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ አስሮ ማቆየትን በሚመለከት ራሱን የቻለ ዝርዝር መግለጫ በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ከአማራ ክልል በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ንጹሃን ለሞት እና አካል መጉደል ጉዳት መጋለጣቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ ወለጋ ዞኖች፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና አርሲ ዞን በኦነግ ሸኔ እና የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል በተካሄደ ግጭት ከ45 በላይ ንጹሃን እንደተገደሉ ተገልጿል፡፡

በጋምቤላ ክልል ደግሞ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከ60 በላይ ንጹሃን በመጠለያ ጣቢያዎች፣ መኖሪያ ቤት፣ በትራንስፖርት እና በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል ተብሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *