ኢትዮጵያ የቁም እንስሳትን ለወጪ ገበያ በባቡር ማጓጓዝ ጀመረች

ኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ወጪ ንግድ ወደ ጅቡቲ በባቡር ለመጀመሪያ ጊዜ ማጓጓዝ ጀመረች

ከዚህ በፊት ወደ ሀገር ዉስጥ ገቢ ምርቶችን ለማስገባት ብቻ ያገለገል የነበረዉ የአዳማ – ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አሁን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የቁም እንስሳትን ማጓጓዝ ጀምሯል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ እንደገለፁት በአዳማ በኩል የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርትን ወደ ውጭ ሀገራት ጥራት ያለውን የስጋ ምርት የመላክ አቅምን ከመጨመሩም ባሻገር የትራንስፖርት መጨናነቅን ይቀንሳል።

ከአዳማ ወደ ጅቡቲ የቁም እንስሳት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ይፋ መሆኑን ያስታወቁት ስራ አስፈፃሚው ይህን አገልግሎት በመጀመራችን አቅማችን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

በባቡር ትራንስፖርት በመጠቀም ወደ ውጭ ሀገራት የሚላከው የእንስሳት ንግድ የህገወጥ ንግድ እንቅስቀሴንን ከማስቀረቱ ባለፈ ጊዜ እና የስጋ ጥራትን እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉም ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በሆነ ህወጥ የእንስሳት ንግድ ዙሪያ ይፋ የተደረገ ጥናት እንደጠቆመው ኢትዮጵያ በቀን ከ1 ሺህ 200 በላይ የቁም እንስሳት በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር በመውጣታቸው በየቀኑ ከ630 ሺህ ዶላር በላይ እንደምታጣ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ሕገ-ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት ሕገ-ወጥ ንግድ በስፋት በሚታይባቸው ዘርፎች ላይ ያካሄዳቸውን ጥናቶች ይፋ አድርጓል።

ጥናቶቹ በቁም እንስሳት፣ በመድኃኒት፣ በጨርቃጨርቅ፣ በሎጂስቲክስ ሥርዓት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችና ንግድን በተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተካሄዱ ናቸው።

በዚህ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ የቁም እንስሳትና የመድኃኒት ሕገ-ወጥ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በጥናቱ ተመላክቷል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ፤ በቁም እንስሳት ኤክስፖርት ግብይት ላይ የሚታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦችን በተመለከተ ጥናት አቅርበዋል።

በዚህም ባለፉት ስምንት ዓመታት ከቁም እንስሳት ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

ለማሳያም ቀደም ሲል ከቁም እንስሳት ንግድ በዓመት እስከ 150 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ በ2023/24 ገቢው ወደ 17 ሚሊየን ዶላር ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል።

የችግሩ ምንጭ የሕገ-ወጥ ንግድ ስልትና ዓይነት እየተቀያየረ መምጣቱ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራው አጥጋቢ አለመሆን፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈና ሕጉን የጠበቀ የግብይት ሥርዓትን ማስተግበር ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጥናቱ አመላክቷል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ልየታና ከተቀባይ አገራት ጋር ያለው ሕጋዊ ስምምነት ላይም ክፍተቶች እንደሚታዩ አንስተዋል።

በመሆኑም በቅርቡ በአገሪቱ በሦስት የመውጫ በሮች በተካሄደ ጥናት በቀን ከ1ሺህ 200 በላይ የቁም እንስሳቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ተረጋግጧል ብለዋል።

በዚህም አንድ የቁም እንስሳት እስከ 530 ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፤ አገሪቱ በቀን 630 ሺህ ዶላር በላይ በአንድ ወር ደግሞ 19 ሚሊየን ዶላር ታጣለች ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አመላክተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *