በአማራ ክልል ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ አብቅቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ምክንያቱን በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ያደረገው እና ለ10 ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ የጊዜ ገደብ በማለቁ በእስር የቆዩ ሰዎች እንዲለቀቁ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በአማራ ክልል በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል ከሚካሄደው የትጥቅ ግጭት ጋር ተያይዞ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ የጊዜ ገደብ በማለቁ በእስር የቆዩ ሰዎች የመልቀቅ ሂደት እንዲቀጥልም አሳስቧል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የነበረው እና ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ለተጨማሪ 4 ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት ዛሬ መጠናቀቁን ኮሚሽኑ አሳትውሷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ እንደቆየ የገለጸው ኮሚሽኑ ከአዋጁ ትግበራ ጋር የተስተዋሉ ክፍተቶችንና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያመላክቱ፣ እንዲሁም ምክረ ሐሳቦችን ያካተቱ መግለጫችን ሲያወጣ የቆየ ሲሆን በዚህም የመንግስት እና ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች በመብት ጥስቶች ላይ መሳተፋቸውን በተደጋጋሚ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በመሆኑም በዚሁ አዋጅ አተገባበር ዐውድ ውስጥ በእስር ላይ የቆዩ ሰዎች እንዲለቀቁ ማድረግን ጨምሮ ወደ መደበኛው የሕግ አተገባበር ሂደት መመለስ፣ እንዲሁም በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ እና ሌሎች ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በዚህ እንዳለ በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ታሥረው የቆዩ ከ80 በላይ ሰዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ከነሐሴ 2015 ዓ .ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ታሥረው የቆዩ ከ80 በላይ ሰዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበዋል።
የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው እነዚህ ሰዎች ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን በአዲስ አበባ እና በአዋሽ አርባ ታስረው የቆዩ ናቸው።
ፍርድ ቤት ከቀረቡት ሰዎች መካከል ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ፖለቲከኞች ይገኙበታል።