ኢትዮጵያ ትልቁን ድልድይ በአባይ ወንዝ ላይ ገነባች

ከስድስት ዓመት በፊት የተጀመረው የአባይ ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡

በአማራ ክልል ጎንደርን እና ጎጃምን የሚያገናኘው የአባይ ድልድይ በቻይናው ሲሲሲሲ የስራ ተቋራጭ ድርጅት የተገነባ ሲሆን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጭ ተደርጎበታል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክቱኢንጂነር ለሚ በቀለ አዲሱ የዓባይ ድልድይ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ በአገራችን ከሚገኙ ድልድዮች የተለየ መሆኑን አስታውቋል።

ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በአንድ ጊዜም ስድስት መኪኖችን ለማስተላለፍ እንዲያስችል ተደርጎ ተገንብቷል ተብሏል።

ድልድዩ በግራና ቀኝ 3 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው የሳይክል መስመር እንዲሁም 5 ሜትር ስፋት ያለው የእግረኛ መንገድ አካቶ እየተሰራ ሲሆን፣ ለከተማዋ እድገትም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር የተገነባው አዲሱ የዓባይ ድልድይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የዓባይ ድልድይ በኢትዮጵያ ከተሰሩ የድልድይ ፕሮጀክቶች በስፋቱም በርዝመቱም ግዙፍ ፕሮጀከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ መንግስት ሁለት ድልድይ ለመገንባት እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመጀመሪያው ልማትን የሚያሳልጥ ድልድይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ህዝብን የሚለያይ ግድግዳ በማፍረስ የአንድነት ድልድይ መገንባት ነው ብለዋል፡፡ 

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች መገኘታቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

ፕሮጀክቱን ተከትሎ ግዙፍ ሕንጻዎች፣ መዝናኛዎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተገነቡ በመሆኑ ፕሮጀክቱ የባህር ዳር ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን ያሳድጋል ተብሏል፡፡

የድልድዩን ግንባታ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ በ2011 ዓ.ም ቢጀመርም በኮቪድና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ለተጨማሪ ሶት ዓመታ ዘግይቷል፡፡

ድልድዩ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የገነባችው ረጅሙ ድልድይ ሲሆን ወደ ግብጽ እና ሱዳን የሚፈሰው የአባይ ወንዝ ማለፊያም ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ 5200 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየገነባች ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

በሀይል የማመንጨት አቅሙ ከአፍሪካ አንደኛ የሆነው ይህ ከ13 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 95 በመቶ ደርሷል፡፡

የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ስራው ግንባታ የደረሰበት ደረጃ 98 ነጥብ 9 በመቶ ተጠናቋል የተባለ ሲሆን የኤሌክትሮ መካኒካ ስራው ደውም በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ከአፍሪካ ግዙፉ ፕሮጀክት የሆነው የህዳሴው ግድብ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ ይገኛል፡፡

አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዉብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመንግስት እና ህዝብ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ643 ሚሊዮን  ብር በላይ ከህዝቡ መሰብሰቡን አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *