በኢትዮጵያ እያሻቀበ ላለው የተረጂዎች ቁጥር ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ መንግስት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች የምግብ ርዳታ ለማቅረብ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ አታለለ አቡሃይ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው የተረጅዎች ብዛት 6 ነጥብ6 ሚሊዮን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ጦርነት እና ሌሎች አደጋዎች ምክንያት የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የብሪታንያ የአፍሪካ ልማት ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የ125 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም አሳሳቢ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር በቀጣይ ወራት 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ይደርሳል ብለዋል።
ድጋፉ ለሶስት ሚሊየን ሰዎች ህይወት አድን እርዳታ ለማቅረብ እንደሚውልም ተገልጿል።
አስቸኳይ ድጋፉ በአልሚ ምግብና ሌሎች ወሳኝ ግብአቶች ምክንያት እየተከሰተ የሚገኘውን ሞት ለመቀነስ ለ75 የጤና ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን ለማቅረብ ነውም ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት ከአንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ በድርቅ እና ግጭቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በጦርነት እና ድርቅ ምክንያቶች ለእርዳታ የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣት ላይ ይገኛል።
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በትግራይና አማራ ክልሎች 400 የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን እንዲሁም 21 ህጻናት ደግሞ ህይወታቸው አልፎ መወለዳቸውን አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ አደጋ እና ሥራ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ብቻ 4 ሚልየን የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቁን ይታወሳል።
ይሁንና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ግን በሀገሪቱ ረሃብ አልተከሰተም በሚል የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ሪፖርት ውድቅ ያደረገ ሲሆን የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች እየረዳሁ ነው ብሏል፡፡