ኑሮ ውድነት በመቀሌ ምን ይመስላል?

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በቆየው ጦርነት ምክንያት ከተጎዱ ክልሎች መካከል አንዱ ትግራይ ሲሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከመሞታቸው በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ይህ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በተደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ጦርነቱ የቆመ ሲሆን አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ዳግም ስራ ጀምረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ከተቋቋመ በኋላ ከፌደራል መንግስት እና ከሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተጎጂዎችን ለመርዳት እየተሰራም ይገኛል፡፡

ቀስ በቀስ ህይወት በትግራይ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶች እየተካሄዱ ሲሆን ኢትዮ ነጋሪ ወደ ክልሉ አምርታ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ምልከታ አድርጋለች፡፡

ከታዘብናቸው ጉዳዮች መካከል ህይወት በትግራይ መዲና መቀሌ ምን ይመስላል? የሚለው ሲሆን የኑሮ ውድነቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያሻቀበ ቢሆንም በትግራይም ይህን አስተውለናል፡፡

ከጦርነት በኋላ መልሶ ማገገም ላይ ያለችው የመቀሌ ከተማ መሠረታዊ ሸቀጦች የሚባሉት ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡

በዚህም ጉዳይ ነጋዴዎችም ሆነ ሸማቾች በዋጋ አለመረጋጋት እና ውድነት እየተማረሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

በከተማዋ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች እና ሸማቾች እንደሚሉት ከሆነ በየእለቱ የዋጋ መቀያየር እና አለመረጋጋት እንዳለ አስረድተዋል። 

ፍራፍሬ ነክ ምርቶች፣ ስጋ እና መሰል ምግቦች ዋጋቸው እንደሚቀያየር አንስተው አሁን ላይ በመቀሌ አንድ ኪሎ ሙዝ በ60 ብር ፣ብርቱካን ከ120 እስከ 140 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ በምልከታችን አረጋግጠናል፡፡

የበሬ ስጋ በኪሎ እስከ 600 መቶ ብር እንደሚሸጥ ያስተዋልን ሲሆን ገበያው ቋሚ የሆነ ዋጋ ስለሌለው በየጊዜው የሚቀያየር እና የሚለዋወጥ መሆኑን ነጋዴዎች አንስተዋል።

በመቀሌ ከተማ ከጦርነቱ በኋላ የገበያው ድባብ በከፍተኛ ሁኔታ ያገገመ መሆኑን የገለጹት ነጋዴዎችና ሸማቾች የገበያው ዋጋ አለመረጋጋት ግን አሳሳቢ እንደሆነባቸው አንስተዋል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የትግራይ ንግድ ቢሮ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ተጠባባቂ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ግዑሽ ወ/ገሪማ በሀገሪቷ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በየቦታው ህገወጥ ኬላዎች እንዲፈጠሩና ምርት አከፋፋዮች አላግባብ ክፍያ እየተጠየቁ በመሆናቸው ወደ መቀሌ ከተማ የሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦች በየእለቱ የዋጋ ጭማሪ እንዲታይባቸው ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

መሠረታዊ ሸቀጣሸቀጦች ወደ ክልሉ ሲገቡ ከ4 በላይ ኬላዎችን እያቋረጡ በመሆኑ ለኪሳራ እና ለመጉላላት እንዲሁም በሸማቾች ላይ አላግባብ የሆነ የዋጋ ጭማሪዎች እንዲደረጉ ምክንያት ሆኗል ሲሉም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ነጋዴዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት በቂ የሆነ ምርት እንዳያመጡ ያደረገ ሲሆን በጥቂቱም ቢሆን ወደ ክልሉ ከሌሎች ቦታዎች እየመጡ ያሉት ጤፍና ሌሎች ምርቶች ሲሆኑ የስንዴ ምርት በአጠቃላይ ወደ ክልሉ እየገባ አለመሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአጠቃላይ እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመኖሩ ምክንያት የክልሉ ነጋዴዎች ምርቶችን ከሌሎች ሀገራት ለማስገባት አዳጋች ሆኗልም ብለዋል።

የክልሉ ንግድ ቢሮው ይህንን ችግር ለመፍታት ምርቶች ለሸማቾች ለማቅረብ ኤግዚቢሽን እና ባዛር በማዘጋጀት ማህበረሰቡን በጥቂቱም ቢሆን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *