በባህርዳር 17 ንጹሃን ዜጎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ከህግ ውጪ መገደላቸው ተገለጸ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ንጹሃንን ከህግ አግባብ ውጪ ገድሏል ብሏል።

ተቋሙ በአማራ ክልል ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ሰፋ ያለ ሪፖርቱን አውጥቷል።

በአቡነ ሃራ፣ ልደታ እና ሳባ ታሚት በተባሉ አካባቢዎች ከ17 በላይ ንጹሃን በመከላከያ ተተኩሶባቸው መገደላቸውን ከአይን እማኞች ማረጋገጡን የጠቆመው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አንዳንድ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች አስከሬን መውሰድ እና መቅበር ተከልክለዋል ተብሏል፡፡

ሪፖርቱ በአማራ ክልል የመከላከያ ሰራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ እንደጀመሩና ከሶስት ወር በኋላ በባህር ዳር ተፈጸሙ የተባሉ ግድያዎችን ብቻ የቃኘ ነው።

የኢንተርኔት አገልግሎት መዘጋት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስከተላቸው ክልከላዎች በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በዝርዝር ለማቅረብ አዳጋች አድርጎታል ብሏል አምነስቲ ኢንተርናሽናል።

ይሁን እንጂ በሪፖርቱ የተካተቱት በባህርዳርም ሆነ በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች በንጹሃን ላይ የተፈጸሙት ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አለማቀፍ ህጎችን የሚተላለፉና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ናቸውም ብሏል።

በተቋሙ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተሩ ቲገር ቻጉታህም “የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ክልል የሚታዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለገለልተኛ አካላት እንዲመረመሩ በአፋጣኝ በሩን ክፍት ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።

በመላ ሀገሪቱ ፍትህ እና ተጠያቂነት እየጠፋ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በአማራ ክልል ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላት በፍጥነት ለህግ እንዲቀርቡ አሳስበዋል።

የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ አለማቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታን እንዲከታተሉ እና ጫና እንዲፈጥሩም ጠይቀዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል አዲሱን ሪፖርቱን ከሁለት ሳምንት በፊት ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ እና ፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መላኩንና እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል።

ተቋሙ ከቅርቡ መንግስት በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ተጠቅሞበታል” የሚል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ወቀሳ ምላሽ ባይሰጥም በተለያየ ጊዜ ድርጅቱ የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።

በነሃሴ ወር 2015 በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት በንጹሃን ላይ የሞት እና የመቁሰል አደጋ እያደረሰ እንደሚገኝ ኢሰመኮን ጨምሮ አለምአቀፍ የመብት ተቋማት በተለያየ ጊዜ ሪፖርት አውጥተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለአራት ወር ያራዘመው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ነፍጥ የታጠቁ አካላት ግጭት አቁመው ለመነጋገር ዝግጁ ከሆኑ ጦርነቱን ለማቆም ፈቃደኝነቱን በተደጋጋሚ ገልጿል።

የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሶ ለማደራጀት በሚል ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዚያ ጀምሮ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጽታ ሀይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ጦርነቱን ተከትሎ የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ከሲቪል አስተዳድር ወደ ወታደራዊ አስተዳድር የተቀየረ ሲሆን ንጹንም ለጅምላ እስር፣ ግድያ እና ሌሎች እንግልቶችን እያስተናገዱ ናቸው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *