የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ መጠየቃቸው ተገልጿል።
ሚንስትሩ ጌዲዮን ይህን ጥያቄ ያቀረቡት፣ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ከሳዑዲ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋሊድ ኤልክረጂ ጋር በተወያዩበት ወቅት መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባሠራጨው መረጃ ገልጧል።
ጌዲዮን፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ለኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች ሕጋዊ የሥራ እድሎችን እንዲያመቻችም መጠየቃቸውን ሚንስቴሩ ጠቅሷል።
ሚንስትር ዋሊድ፣ ሕጋዊ የሠራተኞች ፍልሠት ኢትዮጵያዊያን ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ ቅጥር እድል እንዲያገኙ ለማስቻል አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ተብሏል።
የሳዑዲ ዓረቢያ ፍርድ ቤት ከአደንዛዥ እጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ የሞት ቅጣት የጣለባቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በውይይቱ ወቅት ይነሳ አይነሳ መረጃው አላመለከትም።
በየ ዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን መዳረሻ የሆነችው ሳውዲ አረቢያ በየጊዜው ህገወጥ ዜጎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ታታወቃለች።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በሳውዲ አረቢያ የሞት ፍርድ ለተላለፈባቸው ዜጎች ምህረት እንዲደረግላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
እንደ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ከሆነ ከ60 በላይ ኢትዮጵያውያን የሞት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ተቋሙ የሳውዲ መንግሥት ለኢትዮጵያውያኑ ምህረት እንዲያደርግ የጠየቀ ሲሆን ዜጎቹ በጦርነት፣ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች እና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ምክንያት ከሀገራቸው መሰደዳቸው ከግምት ውስጥ እንዲገባ ሲልም አሳስቧል።
የሳውዲ አረቢያ መንግሥት እስካሁን በእስር ላይ ስላሉ እና የሞት ፍርድ ስለተላለፈባቸው ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በይፋ ያለው ነገር የለም።