በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት በ10 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 8.71 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር አስታውቋል።
በ2018 በጀት ዓመት የ10 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከታቀደው ግብ በላይ ውጤት መመዝገቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 7.25 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፣ 8.71 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል።
የወጪ ንግድ አፈጻጸም ባለፈው ዓመት (2017 ዓ.ም) ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የ6.08 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ43.32 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ሚንስትሩ አብራርተዋል።
ይህ ስኬት በዋናነት በንግድ ዘርፉ ላይ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ውጤት መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ በላኪዎችና በዘርፉ ተዋንያን መካከል የተፈጠረው ጥንካሬ እንዲሁም የልማት አጋሮች ጥረት የታከለበት መሆኑን አመልክተዋል።
በወጪ ንግድ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ተከታታይ ስኬት የሪፎርም ሥራዎች ፍሬ እያፈሩ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ሚንስትሩ ገልጸዋል።
በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥም ገቢውን በማስቀጠል ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ሽግግሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በኢራን እስራኤል ጦርነት ባደረሰው የነዳጅ እጥረት እና መሰል የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዋጋ መቀነስ እና በሀገር ውስጥ ያጋጠሙ የደህንነት ስጋቶች ለገቢው መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።