የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እንዳስታወቀው የኢትዮጲያው ጥቁር ጎፈር አንበሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየተመናመነ በመምጣቱ የመጥፋት አደጋ ተጋረጦበታል ተብሏል፡፡
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት ህገወጥ ዝውውር ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳንኤል ጳውሎስ እንደተናገሩት ህገወጥ የነዋሪዎች ሰፈራ፣ የደን ጭፍጨፋ መኖር፣ የእርሻ ስራ እና ግጦሽ መበራከት የእንስሳቶቹ ስፍራ እንዲወድም ያደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
በዚህም አንበሳን ጨምሮ የዱር እንስሳት የሚፈልጉትን ምግብ እንዳያገኙና በምግብ ሰንሰለት ውስጥ ችግር እንዲፈጠር ብሎም ለህገወጥ አደን በስፋት ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ሲሉ አክለዋል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተለየ የአንበሳ ዝርያ ነው ተብሎ የሚታወቀው እና የመጥፋት አደጋ ያጠላበት የጥቁር ጎፈር አንበሳ ቆዳም በአብዛኛው በኬንያ ፣በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን በኩል የህገወጥ ዝውውር ይከናወንበታል ተብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ ኤዥያ ባሉ የባህል መድኃኒት ቀማሚዎች ዘንድ የነብር እንስሳት ቁጥጥር በመጥበቁ በርካቶች ፊታቸውን ወደ አንበሳ አጥንት ማዞራቸው እንስሳቶቹን ለህገወጥ አደን ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑና ቁጥራቸው እንዲመናመን ማድረጉን አቶ ዳንኤል ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ አንበሶች በህገወጥ አደን ጠፍተዋል ይባል እንጂ አሁን ላይ የቀሩትና ያሉት አንበሶችን ቁጥር ግን በሚገባ ለማወቅ አዳጋች ነው ያሉት ባለሙያው በቂ ጥናት አለመደረጉን እንደ ዋነኛ ምክንያት አንስተዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ከህገወጦች የተያዙ 9 የሚሆኑ አናብስት በማገገሚያ ማእከል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ልዩ ዝርያ ያላቸው የኢትዮጵያ አንበሶች ተገቢው ጥበቃ ካልተደረገላቸውም ሙሉ ለሙሉ የመጥፋት አደጋ ሊጋረጥባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።
ባለስልጣኑ የእንስሳቱን ህልውና ለመታደግ ከፍተኛ የህገወጥ ዝውውር በሚከናወንባቸው ቦታዎች ላይ የቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር ማቀዱን ተናግሯል፡፡
እንደዚሁም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር የምታጠናክርበት የዱር እንስሳት ህግ አተገባበር ኢኒሺየቲቭ አባል መሆኗ ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።
የዝሆኖች መጠለያየሆነው የባቢሌ ፓርክ ከ200 ሄክታር በላይ መሬት ደን እንደወደመ ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ መገለጹ ይታወሳል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኘው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለእርሻ ኢንቨስትመንት በመሰጠቱ ከ200 ሄክታር በላይ የፓርኩ መሬት ደን ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የብሔራዊ ፓርኮች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አዳነ ጸጋዬ፤ የባቢሌን የዝሆኖች መጠለያ ፓርክ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በኩል ለእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰጥቶ ፓርኩ እየታረሰ በመሆኑ፣ በፓርኩ የሚገኙ ዝሆኖች ለአደጋ ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡
የባቢሌን የዝሆኖች መጠለያ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ድንበር ላይ የሚገኝ ሲሆን “በኦሮሚያ ክልል በኩል ያለው የፓርኩ ክፍል ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ አሁንም ድረስ እየታረሰ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የፓርኩ መሬት ለኢንቨስትመንት የተሰጠው ፓርኮችን ለመጠበቅና ለማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን በማያውቅበት መንገድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው አክለውም “ከኹለት ወር በፊት ከኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ተወካይ ጋር በመሆን የፓርኩ ይዞታ እንዳይነካ አካለን የተመለስን ቢሆንም፤ ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት የፓርኩ ውስጣዊ ክፍል እየታረሰ ነው” ብለዋል።