በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥማል መባሉን ብሔራዊ ባንክ አስተባበለ

በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥማል መባሉን ብሔራዊ ባንክ አስተባብሏል።

በኢትዮጵያ በተለይም የግል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳጋጠማቸው በተለያየ መልኩ ሲገለጹ ቆይቷል።

የባንክ ደንበኞችም ለአገልግሎት ባመሩባቸው የግል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ ሲጠይቁ እንዳልሰጧቸው በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

በስድስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባኤ እየተሰተፈ የሚገኘው ብሔራዊ ባንክ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ምላሽ ሰጥቷል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ እንዳሉት “በኢትዮጵያ በግል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ገጥሟቸዋል እሚባለው መረጃ ሀሰት ነው” ብለዋል።

የጥሬ ገንዘብ እጥረት ገጥሟቸዋል የተባሉት አምስት ባንኮች ናቸው መባሉን ሰምተናል ፣ “ነገር ግን በሶስት ባንኮች ላይ የተወሰነ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ገጥሞ ነበር፣ ብሔራዊ ባንክ እና ሌሎች ተቋማት በወሰዷቸው ማስተካከያዎች አሁን ላይ ከአንድ ባንክ በስተቀር የጥሬ ገንዘብ እጥረት ያጋጠመው ባንክ የለም” ሲሉም ምክትል ገዢው አክለዋል።

በኢትዮጵያ የገንዘብ አቅርቦቱ እና ፍላጎቱ የተጣጣመ አይደለም ያሉት አቶ ሰለሞን አሁን ያጋጠመው ክስተትም ጦርነት ውስጥ በነበርንበት የቆመው የፋይናንስ እንቅስቃሴ አሁን የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የፋይናንስ ፍላጎቱ በመጨመሩ ብቻ የተፈጠረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎቶችን ለዓለም አቀፍ ተቋማት በሯን ክፍት ማድረጓን ተከትሎ ይህ ሂደት የት ደረሰ? በሚል ለምክትል ገዢው ለቀረበላቸው ጥያቄም “ስራው ሰፊ ዝግጅቶችን የሚጠይቅ ነው፣ ከዓለም ባንክ ጋርም አብረን እየሰራን ነው በአንድ ዓመት ውስጥም ስራውን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

“የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱን ተከትሎ የአገር ውስጥ ባንኮች ራሳቸውን ተወዳዳሪ ለማድረግ ውህደት ለመፈጸም በሂደት ላይ ያሉ ባንኮች አሉ” ያሉት አቶ ሰለሞን የኢትዮጵያ ባንኮች በቴክኖሎጂ ፣ ፋይናንስ አቅም እና ሰው ሀይል የበለጠ እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል።

ስድስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን ትኩረቱን በካፒታል ማርኬት ላይ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *