በሰሜን ኢትዮጵያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸው ተገለጸ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም በያዝነው ዓመት ሕዳር ወር የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡

ይሁንና የሰላም ስምምነት ቢፈረምም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ የሕፃናት አድን ድርጅት/ሴቭ ዘ ችልድረን አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ለኢትዮ ነጋሪ በላከው መግለጫ እንዳለው የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ ያስፈልጋል ብሏል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕፃናት በላይ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ይህም እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ 16 ኢትዮጵያውያን ሕፃናት መሃከል አንዱ ከትምህርት ገበታ መገለሉን ያሳያል ተብሏል፡፡

ይህ አሃዝ ኢትዮጵያን ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቀውስ ካስተናገዱ ሃገራት አንዷ እንደሚያደርጋት ተገልጿል፡፡ 

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳትመድረሱን በትምህርት ሚኒስቴር፣ በሴቭ ዘችልድረን እና ዩኒሴፍ የሚመራው የትምህርት ክላስተር ያወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ ያሳያል። 

በተለይ በትግራይ 85 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከባድ ወይም ከፊል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሁሉም የህዝብ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ናቸው፡፡

ይህም በክልሉ 2.3 ሚሊዮን የሚገመቱ ህጻናት በኮቪድ ወረርሽን ጀምሮ የሁለት አመቱ ጦርነት ሲታከልበት ለሶሰት አመታት ከትምህርት እንዲገለሉ ያደረገ ሲሆን 22 ሺህ 500 መምህራን ያለ ደሞዝ ከሁለት አመት በላይ ቆይተዋል ተብሏል፡፡

ለረጅም ጊዜ ከትምህርት ቤት የራቁ ሕፃናት ለበርካታ የመብት ጥሰት እና ብዝበዛ አንዲሁም ጥቃት የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል፡፡ 

ዝናሽ * የ13 አመት ታዳጊ ስትሆን በአማራ ክልል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነች።

ቤተሰቦቿ በአነስተኛ ግብርና እና በከብት እርባታ የሚተዳደሩ ሲሆን በአከባቢው በተነሳው ጦርነት ሳቢያ ቤታቸውን እና አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፣ በዚህም ምክንያት ለአንድ አመት ትምህርቷን አቋርጣለች። አሁን ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ከቻሉ ጥቂት ልጆች አንዷ ነች፡፡ 

“ከአንድ ዓመት በፊት እኔና ቤተሰቤ በአካባቢያችን በተነሳው ጦርነት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያችን አምልጠን ሸሸን። በግጭቱ ቤቶች ወድመዋል፣ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል በርካቶችም ተሰደዋል። አሁን ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ትምህርቴን መቀጠል ችዬ በአቅራቢያችን በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ። 

የህፃናት አድን ድርጅት በጦርነት ሳቢያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ህጻናት ባሉበት ስፍራ ደህንነቱ የተጠበቀ የመጫወቻ እና መማሪያ ስፍራዎችን በማሰናዳት፣ ስሜታቸውን ጤናማ በሆነ መልኩ እንዲገልጹ እና የስነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ሰራዎችን እያከናወነ መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያን የዚህ አመት ሰብአዊ እርዳታ ጥያቄ ለማሟላት ያስፈልጋል ብሎ ከጠየቀው የገንዘብ መጠን 18.4% ብቻ የሚያሟላ የገንዘብ ድጋፍ የተሰበሰበ ሲሆን እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለመደገፍ ተጨማሪ 3.26 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል። 

በኢትዮጵያ የህጻናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ጅልድረን) ዋና ዳይሬክተር ዣቪየር ጁበርት በበኩላቸው “በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታዩት የከፋው ነው።ግጭት፣ ረሃብ እና የአየር ንብረት ቀውሱ ተፅእኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏቸዋል፣ በዚህም ምክንያት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ህጻናት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል”  ብለዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *