ሕወሀት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ከ22 ወራት በኋላ ውሳኔው ተሽሯል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኛ ድርጅት እንዲሠረዝ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባሄደው ልዩ ስብሰባ ህወሓትን ከሽብርተኛ መዝገብ ለማንሳት በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
ለሰሜኑ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።
በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረትም በፌደራል መንግስት እና በህወሓት በኩል ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ስምምነቱ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለተጎጂዎች እንዲቀርብ አድርጓል።
ህወሓትም ታጣቂዎቹን ወደ ካምፕ በመሰብሰብ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ማስረከቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ላይ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሀትን ከሽብርተኝነት መዝገብ ዝርዝር ውስጥ እንዲነሳ ወስኗል።
በምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ላይ 280 የፓርላማ አባላት እንደተገኙ ሲገለጽ የውሳኔ ሀሳቡ በ214 ድጋፍ በ61 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል ተብሏል።
አምስት የምክር ቤቱ አባላት ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ እንዳደረጉ ተገልጿል።
ህወሀት በሀገር መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ይገኝ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ነበር ግንቦት 2013 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው።