የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባቀረበው ጥያቄና ከተለያዩ አካላት ጋር ባደረገው ጥረት፣ ከ600 በላይ ሰዎች ከእስር መፈታታቸውን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸው እና ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ዜጎች ጉዳያቸው በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ጥያቄ አቅርበዋል።
ኢሰመኮም ይህንን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ለመንግሥት ማቅረቡን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ እንደገለጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉዳዩን በአዎንታ ተቀብለው፣ የሕግ የበላይነትን በጠበቀ መልኩ ለሰላም፣ ለሀገራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲ የሚያግዙ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች አቅጣጫ ሰጥተዋል ተብሏል።
በዚህ መሠረት በተቀመጠው የሕግና የይቅርታ ሂደት መሠረት፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸው በይቅርታ እንዲፈቱ፣ በክስ ሂደት ላይ ያሉ ተከሳሾችም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ ተወስኗል ሲል ኢሰመኮ ገልጿል።
ከእስር ከተለቀቁት ውስጥም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲን ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶክተር ካሳ ተሻገር፣ የቀድሞው የኢዜማ ሊቀመንበር ዶክተር ከበደ ጫኔ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ኢሰመኮ ይህንን ውሳኔ ለሰላም፣ ለሀገራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ጠቃሚ እርምጃ በማለት አድንቋል። በቀጣይም ተመሳሳይ የሰላም ግንባታ ጥረቶች እንዲጠናከሩም ጠይቋል።
ከእስር የተለቀቁት ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው በመመለስ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ በሀገራዊ የሰላም ግንባታና ልማት ላይ እንዲሳተፉም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮች በትጥቅ ትግል ይፈታሉ ብለው የሚያምኑ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡም ኢሰመኮ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ በተጨማሪም በአዲስ አመት ዋዜማ ከእስር የተለቀቁት ዜጎች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲቀላቀሉ የሚደረገውን የማቋቋም ሥራ የመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ አካላት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርቧል።
ይሁንና ከአማራ ክልል ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ካሉ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች በተለይም መንግሥት አዘጋጅቶታል የተባለን ሰነድ ለመፈረም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ከእስር አልተለቀቁም።