የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ስምረት (ስምረት)፣ በትግራይ ፖለቲካ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ህወሀት በሀይል ስልጣን መቆጣጠሩን አስታውቋል።
በትግራይ ክልል ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው ሀይል ክልሉን ወደ ከፋ የጦርነት ድባብና “ሰው አልባ” መዋቅር እየመራው መሆኑንም አስታውቋል።
ፓርቲው የድርጅቱ ምክር ቤት ከግንቦት 29 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ያካሄደውን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ክልል እየተባባሰ መጥቷል ያለው “የኋላ ቀር ቡድን” ውሳኔ የህልውና አደጋ እየደገነ መሆኑን አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ የወጣቶች እፈሳ፣ ከፍተኛ የስደት ፍሰት፣ የምሁራን መበተን እና ከባድ የኑሮ ውድነት መንገሱን ድርጅቱ በዝርዝር አስረድቷል።
የስምረት ምክር ቤት በመግለጫው፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ሥልጣን ላይ ያለው “ኋላ ቀር ቡድን የኤርትራን መንግሥት የወታደራዊ መመልመያ ፖሊሲ በክልሉ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።” ይህ ድርጊትም በትግራይ ላይ ከባድ የጦርነት ድባብና የጦርነት ወሬ እንዲነግስ ማድረጉን ጠቅሷል።
ሰሞኑን “በታሕታይ አድያቦ አካባቢ በገምሃሎ” በተባለ ስፍራ በደረሰው የድሮን ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ወጣቶችን እልቂት የተሰማውን ሀዘንም ገልጿል።
ለዚህ የድሮን ጥቃት እና ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂው ገዥው ቡድን መሆኑን በይፋ ከስሷል። ይህ “ቡድን የትግራይ ወጣቶችን ወደ ሱዳን አሻግሮ በውክልና ጦርነት ውስጥ እንዲማገዱና በሕይወታቸው ቁማር ለመጫወት ባስተላለፈው ጨካኝ ውሳኔ ምክንያት እልቂቱ ተከስቷል” ብሏል።
በመሪነት ላይ ያለው ኃይል አሁንም ለሥልጣኑ ሲል ሕዝብን በፕሮፓጋንዳ እያደናገረ ወደ ሞት እየነዳው ነው ያለው ስምረት ፓርቲ፣ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ አሁን ክልሉን በጠመንጃ አፈሙዝ ይዞ ያለው ኃይል መሆኑን ሕዝቡ በአንድ ድምፅ ሊነግረው እንደሚገባም አሳስቧል።
በመጨረሻም የትግራይ ወጣቶች ከዚህ “የሞት ግብዣ” እና ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ ለመሆን ከሚንቀሳቀሰው ኃይል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ሕይወታቸውን እንዲታደጉ ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል። ችግሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሕዝቡና ወጣቱ ከትግራይ ዲሞክራሲያዊ ስምረት (ስምረት) ጎን ተሰልፈው እንዲታገሉ በማሳሰብ መግለጫውን ቋጭቷል፡፡
ህጋዊነቱ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሀት ባሳለፍነው ቅዳሜ ማምሻ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ጸጥታ ሀይሎች ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ጉዳት መድረሱን መግለጹ ይታወሳል።
የፌደራል መንግሥት እስካሁን ከሰሞኑ በትግራይ ተፈጽመዋል በተባሉ የድሮን ጥቃቶች ዙሪያ ያለው ነገር የለም።