በኢትዮጵያ የስሪላንካ ኤምባሲ ተወካይ ግንቦት 23/2026 ለስራ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሦስት ዜጎቹ እንደተሰወሩ እና ሲሪላንካ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተደውሎ እያንዳንዳቸው 30 ሺ ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ግንቦት 26 ቀን 2026 በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ሪፖርት አደረጉ።
በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ምክትል ዋና ጠቅላይ መምሪያ ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትልና የምርመራ ቡድን በማዋቀር ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደገለጸው ከሌሎች የፀጥታ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ባሰባሰበው መረጃ ሦስቱ ግለሰቦች በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2C- 40463/AA በሆነች ሱዚኪ ዲዛየር መኪና ከኤርፖርት ተሳፍረው መሄዳቸውን አረጋግጧል።
የክትትል ቡድኑ አባላት አሽከርካሪውን ጨምሮ 2 ኢትዮጵያውያንን እና 4 የፓኪስታን ዜግነት ያላቸውን 6 ወንጀል ፈፃሚዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡
ወንጀል ፈፃሚዎቹ ሦስቱን የሲሪላንካ ዜጎች በሻሸመኔ ከተማ ወረዳ ቡቄ ቀበሌ 4 ልዩ ቦታው ደራርቱ ሆቴል ጀርባ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ አንድ ክፍል ውስጥ ዘግተውባቸው እንደተገኙ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቆ ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተሰራው ስራ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ በኦሮሚያ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንዲሁም የአዳማ ፈጣን መንገድ ኢንተርፕራይዝ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገልጾ ለተቋማቱ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ፖሊስ በቀጣይ የወንጀሉን ምርመራ እንደሚቀጥል ገልጾ ተጨማሪ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።