ተቋሙ የስነ ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል ያላቸውን 1 ሺህ 139 ሠራተኞች ላይ እርምጃመውሰዱን አስታውቋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ኃላፊዎችና ሠራተኞች መካከል 16 ሲሰናበቱ፤ 721 የደሞዝ ቅጣት የተቀጡ እንዲሁም 402 የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ናቸው፡፡
አገልግሎቱ በ1 ሺህ 139 ሠራተኞች ላይ ከወሰዳቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች መካከል 103 ሠራተኞች ላይ በደንበኞች የቀረበን ጥቆማ በመመርመር የወሰደው ሲሆን ቀሪ 1 ሺህ 36ቱ ተቋሙ በራሱ ግኝት አጣርቶ የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት አገልግሎቱ በሙስና መጠቆሚያ ዘመናዊ መተግበሪያ (Corruption Reporting App) እና በሌሎች አማራጮች ከደንበኞቹ የደረሱትን 427 ጥቆማዎችን መርምሮ በ103 ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስጃለሁ ብሏል፡፡
በደንበኞቹ በቀረቡት ጥቆማዎች መሰረት 14 የፅሁፍ፣ 80 የደሞዝ ቅጣት፣ 2 ከቦታ የማንሳትና 7 ስንብት በድምሩ 103 እርምጃዎች ተወስዷል፡፡
የብልሹ አሰራር ጥቆማ ከቀረበባቸው ጉዳዮች መካከል የአዲስ ቆጣሪ ጥያቄ፣ የኃይል መቆራረጥና አስቸኳይ ጥገና፣ የቆጣሪ ንባብና የቢል ስብሰባ እንዲሁም ንብረት አያያዝና አጠቃቀም ይገኙበታል፡፡
ደንበኞች አሁንም የዲጂታል የብልሹ አሰራር ጥቆማ መቀበያ(www.eeuethics.et) በመጠቀም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮችን እንዲጠቁሙ አገልግሎቱ ያበረታታል፡፡
አገልግሎቱም ማንኛውም የህግና የሥነምግባር ጥሰት ድርጊቶችን ለሚያጋልጡ ጠቋሚዎች እውቅና የሚሰጥ ሲሆን፤ ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ በነፃነትና በተነሳሽነት የሙስና ወንጀሎችን እንዲያጋልጡ ጥሪውን አቅርቧል።
ደንበኞች በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 መሰረት ህጋዊ ከለላ የማግኘት መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአገልግሎቱ አሰራርና መመሪያ መሰረት ጠቋሚዎች የሚያቀርቡት ህጋዊ ጥያቄ ያለተጽዕኖ እንዲስተናገዱ ተገቢውን ከለላና ጥበቃ ይሰጣል፡፡