በነጻ የንግድ ቀጠናዎች ያሉ ነጋዴዎች ከግብር ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ተወሰነ

በነጻ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ ግብአቶችን እና ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ ተወሰነ::

የገንዘብ ሚኒስቴር ለገቢዎች ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ምክንያት ከሆኑት መካከል የካፒታል እጥረት፤ የግብአት አቅርቦት ችግር  እና የባለሙያ እጥረት በዋንኛነት ምክንያት አስቀምጧል፡፡

እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በማቃለል የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ልማትን  ማሳደግ አእንደሚገባ በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል፡፡

ግብአቶች እና ሌሎችም ምርቶች በበቂ መጠን ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ አስመጪዎች ምርቱን ለገበያ ከማቅረባቸው በፊት የሚከፍሉት ቀረጥ እና ታክስ ውስን የሆነውን ካፒታላቸውን በመያዝ ረገድ የሚያሳድረባቸውን ጫና ማቃለል እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

አስመጪዎች  ግብቶችን  እና ምርቶችን ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፍሉ ወደ አገር ውስጥ አስገብተው ለግብአቱ ወይም ለምርቱ ገበያ ባገኙ ጊዜ ቀረጥ እና ታክሱን የሚከፍሉበትን አሰራር የሚፈቅድ የነጻ የንግድ ቀጠና አሰራር መዘርጋቱንና  ይህንን ስርአት የሚያስፈጸሙ ነጻ የንግድ ቀጠናዎች በየካባቢው የተቋቋሙ መሆኑ አስታውሷል::

ከዚህም በተጨማሪ ከዛሬ ሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በነጻ ንግድ ቀጠና ውስጥ ተሰማርተው ግብአቶችን እና ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ መፈቀዱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በነጻ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ሲሩ የነበሩ ኩባንያዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እና ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት በሰራተኞች ፍልሰት፣ የገንዘብ አቅርቦት እና ሌሎች የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ማነስ ምክንያት ስራቸው እየተጎዳ መሆኑን እና ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የመንግስት ከፍተኛ ሃለፊዎችም የኢንቨስተሮቹን ጥያቄ መንግስት እንደሚረዳ እና በቀጣይ ሌሎች ድጋፎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *