ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ባለአክሲዮኖችን ለመመዘን አዲስ መመሪያ አወጣ

ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲስ መመሪያ በኢንሹራንስ ዘርፉ ላይ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና የተጠናከረ የኮርፖሬት አስተዳደርን ለማስፈን ያለመ ነው ብሏል።

በዚህ መመሪያ መሠረትም ማንኛውም የኢንሹራንስ ኩባንያ የቦርድ አባላት ስብጥር አንድን ጾታ ብቻ የያዘ መሆን የለበትም።

እያንዳንዱ የኢንሹራንስ ኩባንያ ቢያንስ ሁለት ሴት የቦርድ አባላት ሊኖሩት እንደሚገባ መመሪያው የግዴታ መስፈርትን አስቀምጧል።

በተጨማሪም አንድ የቦርድ አባል ለመሆን ዝቅተኛው የዕድሜ ገደብ 30 ዓመት መሆን እንዳለበት ተደንግጓል።

እያንዳንዱ የኢንሹራንስ ኩባንያ ሦስት ገለልተኛ የቦርድ አባላት ሊኖሩት ይገባል የተባለ ሲሆን እነዚህ ግለሰቦች የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እና በፋይናንስ ዘርፍ ወይም ተያያዥ መስኮች የ10 ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል ተብሏል።

እንደ መመሪያው ከሆነ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች በገለልተኛ የቦርድ አባልነት ሊመረጡ ይችላሉ።

አንድ ግለሰብ የኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ ለመሾም በኢንሹራንስ ዘርፍ ቢያንስ የ12 ዓመት የሥራ ልምድ ሊኖረው እንደሚገባ ተደንግጓል።

ከዚህ ውስጥ ቢያንስ አምስት ዓመቱን በከፍተኛ የሥራ መሪነት ደረጃ የሰራ መሆን ይኖርበታል ተብሏል።

ትምህርትን በተመለከተ ዝቅተኛው መመዘኛ የመጀመሪያ ዲግሪ ወይም በኢንሹራንስ ሙያ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ዲፕሎማ (CII) እንዲኖረው ይጠይቃል።

የወንጀል ሪከርድ ያለባቸው፣ በሙስና ወይም በማጭበርበር ድርጊት የተሰማሩ ግለሰቦች በዘርፉ አመራር መሆን እንደማይችሉ ተጠቅሷል።

በፋይናንስ ረገድም ግለሰቡ የከሰረ ወይም በባንክ ዕዳ ምክንያት ንብረቱ የተያዘበት መሆን እብደሌለበትም በዚህ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ላይ ተጠቅሷል።

ኩባንያዎች ስለ አመራሮቻቸው ብቃት ጥርጣሬ ሲኖራቸው ወዲያውኑ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያሳውቁም ያስገድዳል።

እንዲሁም የጥቆማ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው መመሪያው የሚያዝ ሲሆን የከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎችን ሹመት በተመለከተ መመሪያው በሚጠይቀው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፈቃድ ያልጠየቁ ኩባንያዎች ለእያንዳንዱ የሥራ መደብ የ10,000 ብር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ይህ መመሪያ “በኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ተፅዕኖ ያላቸው ግለሰቦች መመዘኛ መመሪያ ቁጥር SIB/63/2026” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ከዛሬ ከመጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የጸና እንደሚሆን ከመመሪያው ተረድተናል።

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ምክረ ሀሳብ አማካኝነት የገንዘብ ፖሊሲዎቿብ እያሻሻለች ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ዋነኛው ተቋም ሆኗል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *