የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት የ137 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እያስተናገደ መሆኑን ገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእስራኤል-ኢራን ጦርነት ምክንያት በሳምንት የ137 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እያስተናገደ መሆኑን ገለጸ

ከሰባት ቀናት በፊት የተጀመረው የእስራኤል-ኢራን ጦርነት ጉዳቱ በመላው ዓለም ላይ ሲሆን ኢትዮጵያም የጦርነቱ ተጎጂ ሆኗ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳስታወቀው በዚህ ጦርነት ምክንያት በየሳምንቱ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የካርጎ በረራን ሳይጨምር የመንገደኞችን ብቻ 101 በላይ በረራዎችን እየሰረዘ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በረራዎቹ በመሰረዛቸው ምክንያትም እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር በማጣት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ የእስራኤል- ኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በቀን ወደ ዱባይ ሦስት ጊዜ ፣ ወደ ሻርጃ አንድ ጊዜ፣ ወደ እስራኤል ሦስት ጊዜ፣ ወደ አቡዳቢ፣ ወደ አማን ሁለቴ መንገደኞችን ያመላልስ ነበር።

በጦርነቱ ምክንያት አየር መንገዱ በአማካኝ በየዕለቱ 15 በረራዎችን እየሰረዘ መሆኑን ገልጾ ይህም ገቢ እያሳጣው መሆኑን አስታውቋል፡፡

የካርጎ ወይም እቃ ጭነቶችን በተመለከተ ደግሞ በየቀኑ ወደ እያንዳንዱ ሀገር አንድ ጊዜ የጭነት በረራዎችን ያደርግ እንደነበር የገለጸው አየር መንገዱ በድምሩ በሳምንት 160 በረራዎችን ለመሰረዝ እንደሚገደድ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አየር መንገዱ “በሳምንት ከ45 እስከ 50 ሺሕ መንገደኛ እናጓጉዛለን” ያለው ተቋሙ፣ ጦርነቱ ከቀጠለ ከመንገደኞች ጉዞ “135 ሚሊዮን ዶላር ገደማ”፤ ከጭነት አገልግሎት ደግሞ “ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ልናጣ እንችላለን” ሲልም ተናግሯል።

አየር መንገዱ የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ወደ ኦማን፣ቤሩት፣ ባህሬን፣ ቴልአቪቭ፣ ዶሃ፣ ኩዌት፣ ዱባይ፣ ሻጃህ፣ አቡዳቢ እና ዳማም ከተሞች በረራዎቹን ጦርነቱን ተከትሎ የአየር ክልሎች በመዘጋታቸው በረራዎቹን ላልተወሰነ ጊዜ እንዳቋረጠ አስታውቋል፡፡

እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመላው ዓለም ከ23 ሺህ በላይ በረራዎች ተሰርዘዋል፡፡

የአየር መንገዱ ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በግማሽ ዓመት ውስጥ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጸው ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የካርጎ ጭነት የ1 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ አለውም ተብሏል፡፡

10 ሚሊዮን መንገደኞችን እንዳጓጓዘ የገለጸው አየር መንገዱ የእስራኤል-ኢራን ጦርነት ከተራዘመ በገቢው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ይገመታል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *