መንግስት በኦሮሚያ ክልል አርሲ በቂ የጸጥታ ሀይል እንዲያሰማራ ኢሰመኮ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ንጹሃን ዜጎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ እን ዳስታወቀው በዞኑ ያለው ሁኔታ ለተወሰኑ ጊዜያት እየተሻሻለ የነበረ ቢመስልም ከጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ታጣቂ ቡድኑ በሽርካ፣ በጉና፣ በመርቲ፣ በአሰኮ እና በኦንቆሌ ዋቤ ወረዳዎች በሰዎች ላይ በፈጸማቸው ጥቃቶች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል፡፡

እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የደህንነት ሥጋቶች ምክንያት የነዋሪዎች መፈናቀል መከሰቱን ኢሰመኮ የደረሱትን ጥቆማዎችና አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ነዋሪዎችን እና የየአካባቢዎቹን የመንግሥት ኃላፊዎች በማነጋገር ባሰባሰባቸው መረጃዎች ማረጋገጡን አስታውቋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በዞኑ ሽርካ ወረዳ ጃዊ ቀበሌ እና በሮቤ ወረዳ ገባ ቀበሌ በፈጸመው ጥቃት ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ቁጥራቸው በውል ባልተለዩ ሰዎች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ አካል ጉዳት፣ እገታ እንዲሁም መፈናቀል መድረሱን ኢሰመኮ በተለያዩ መንገዶች ባሰባሰባቸው መረጃዎች አረጋግጧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች የሚፈጸመው ጥቃት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት የሆኑት በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ጉዳቶች፣ ማፈናቀሎች፣ እገታዎች እንዲሁም የንብረት ውድመቶችና ዘረፋዎች የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ጨምሮ ነዋሪዎች በሰላምና በደህንነት የዕለት ተዕለት ተግባራትን እንዳያከናውኑ አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥታት በተደጋጋሚ ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው እና የጥቃት ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች በቂ የጸጥታ አካላትን እንዲያሰማሩ አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲያመቻቹ እንዲሁም ተመሳሳይ ጥቃቶችን ቀድሞ የመተንበይና የመከላከል ሥራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በያዝነው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ከ30 በላይ የዕምነቱ ተከታዮች መገደላቸውን እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ለአካል መጉደል እና ንብረታቸው መዘረፉን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት በበኩሉ ጥቃቱን በማውገዝ መንግስት የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት እንዲያስከብር መጠየቁም ይታወሳል፡፡

የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግስት እስካሁን በግድያው ዙሪያ ያወጡት መግለጫ የለም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *