የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው በቻይና እስር ቤት ለረጅም ጊዜ በሞት ፍርድ ጥላ ስር የምትገኘውን ኢትዮጵያዊቷን ናዝራዊት አበራን ወደ ሀገሯ ለመመለስ መፍትሔ ይሰጣል የተባለለትን የፍርደኞች ማስተላለፍ ስምምነት አዋጅ አፅድቋል።
ምክር ቤቱ ይህንን ስምምነት ያጸደቀው ከቻይና በተጨማሪ ከብራዚል ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ጋር የተደረገውን የፍርደኞች ማስተላለፍ እና ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተፈረመውን በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነቶችን ጨምሮ ነው።
በውይይቱ ወቅት በተለይም ከቻይና ጋር የተደረገው ስምምነት ለዓመታት በፍርድ ሂደት ላይ የምትገኘውን ናዝራዊት አበራን ጉዳይ በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚሆን ተገልጿል።
ይሁን እንጂ በዕለቱ የምክር ቤት አባላት በስምምነቱ ላይ የተለያዩ አመለካከቶችን ያነሱ ሲሆን የሁለቱ ወገኖች የክርክር ነጥብም የአዋጁን አስፈላጊነትና የሉዓላዊነት ጥያቄን ያገናዘበ ነበር።
የፓርላማ አባሉ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በሀገሪቱ ውስጥ በሕገ-ወጥ ማዕድንና በገንዘብ ማጠብ ወንጀል የሚሳተፉ የቻይና ዜጎች በስፋት መኖራቸውን በመጥቀስ፣ እነዚህ ግለሰቦች በሀገር ውስጥ ሕግ ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ እንደሚገባ ሞግተዋል።
አባሉ አክለውም፤ መሰል ስምምነቶች ከምሥራቃዊያን ሀገራት ባለፈ ከምዕራባውያን ጋር ለምን እንደማይደረጉና በዚያ በኩል የሚፈለጉ ወንጀለኞች ስለመኖራቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
በአንፃሩ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ ለተነሱት ስጋቶች በሰጡት ምላሽ፣ አዋጁ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈ ግልጽ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ የታለመ መሆኑን አስረድተዋል።
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት እኩል ፈቃድ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አንዱ ሀገር በሌላው ላይ የሚጭነው ተፅዕኖ እንደሌለ የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ቀደም ሲል በዲፕሎማሲያዊ ጥረት በርካታ ፍርደኞች ወደ ሀገር መመለሳቸውንና አሁን የጸደቀው ሕግ ግን አሰራሩን ሥርዓት ለማስያዝ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን የሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።