ኢትዮጵያ ከቻይና ያለባትን ዕዳ ወደ ዩዋን እንዲቀየር ጠየቀች

ኢትዮጵያ ለቻይና መንግሥት የምትከፍለውን ቢያንስ 5.38 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ በከፊል ወደ ቻይና ገንዘብ (ዩዋን) ለመቀየር ከቤጂንግ ጋር ውይይት መጀመሯ ተዘግቧል።

ይህ እርምጃ ቀደም ሲል ኬንያ ያደረገችውን በመከተል፣ ቻይና የገንዘብ ምንዛሪዋን ዓለም አቀፋዊ የማድረግ ጥረቷን የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።

ብሉምበርግ እንደዘገበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ እዮብ ተካለኝ ባለፈው ወር ወደ ቤጂንግ ባደረጉት ጉብኝት ከቻይና ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ እና ከቻይና ሕዝብ ባንክ ጋር ለዚህ እምቅ የዕዳ ልውውጥ ውይይት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ገዥው ይህንን የገለጹት አርብ ጥቅምት 07 ቀን 2018 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (IMF) ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው።

ሀገሪቷ ዕዳውን በዩዋን መክፈል የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ያለውን ጫና በማቅለል እና በአሜሪካ ዶላር የምንዛሪ ተመን መለዋወጥ ሳቢያ የሚመጣውን ስጋት ለመቀነስ ይረዳታል ተብሎ ይታመናል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ እዳ እንዳለባት የዓለም ባንክ ሪፖርት ያስረዳል።

ከሁለት ትሪሊዮን ብር በላይ የሀገር ውስጥ እዳ ያለባት ኢትዮጵያ እያንዳንዱ ዜጋዋ የ570 ዶላር እዳ እንዳለበት ያስረዳል፡፡

ቻይና፣ የዓለም ባንክ፣ አድሪካ ልማት ባንክ፣ አይኤምኤፍ እና ሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት ለኢትዮጵያ ብድር ያቀረቡ ሀገራት እና ተቋማት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት በዋሸንግተን በተካሄደው የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የብድር እንዲሰጣት ጥያቄ አቅርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድና ልዑካቸው ከዓለም ባንክ ምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ኒዲያሜ ዲኦፕ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ሚኒስትሩ በግብርና ምርታማነት፣ በኢነርጂ፣ በሰው ሀብት ልማት፣ በቀጣናዊ ትስስርና መሠረተ ልማት ከፍ ያለ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መጠየቃቸውን ሚኒስቴሩ በድረ ገጹ ላይ ያጋራው ጽሁፍ ያስረዳል፡፡

አቶ አህመድ የዓለም ባንክ ላደረገው ከፍተኛ ቴክኒካዊና የፋይናንስ ድጋፍ እንዳመሠገኑ፣ መንግሥት እያካሄዳቸው ያሉ ደሃ ተኮር ሪፎርሞችን በተመለከተ ማብራራታቸውንና ሪፎርሙን ለማስቀጠል የዓለም ባንክ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸውን አክሏል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቷ ይታወሳል።

ይህ የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ ዙሮች ለኢትዮጵያ በመለቀቅ ላይ ሲሆን የገንዘብ ድጋፉ ከውጭ ምንዛሬ ተመን ፖሊሲ ማሻሻያ ጋር የተገናኘ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *