አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲን ለማሸነፍ ህብረት ፈጠሩ

ፓርቲዎቹ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘ የቅንጅት ፖርቲ መመስረታቸውን ገልጸዋል።

ላለፉት ሥስት ዓመታት በትብብር በጋራ ሲሠሩ የቆዩት አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት መመሥረታቸውን በዛሬው ዕለት አስታውቀዋል።

የቅንጅቱ ስያሜም “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” መሆኑን በዛሬው የመስራች ጉባኤ ላይ ተገልጿል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ እናት ፖርቲ ፣የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፖርቲ (ኢሕአፓ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ናቸው ቅንጅት መመሥረታቸውን አስታውቀዋል።

ቅንጅቱንም እንዲመሩ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝዳንት አቶ አብርሀም ጌጡ ተመርጠዋል።

“ለእናት ፖርቲ ትልቅ ቀን ነው” ያሉት የፖርቲው ፕሬዝዳንት ሰይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር)፤ “ኢትዮጵያ 50 ዓመታት የተበታተነ የፖለቲካ ጎራ መከራ እየወረደበት ላለው ፖለቲካ መፍትሄ የሚሰጥ ቅንጅት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በተናጥል የሚመጣ ለውጥ የለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ቅንጅት መመስረቱ አማራጭ የሌለው ተግባር ነው ብለዋል።

ፓርቲዎቹ ቅንጅት የመሠረቱት ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ታካሂዳለች ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።

ሌላዉ የቅንጅቱ መስራችና የትብብሩ አባል ፖርቲ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን) መስራችና ፕሬዝዳንት አቶ ምርጫው ስንሻው፤ “በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ የተደቀነበትን የህልዉና አደጋ ለመታገል ቅንጅት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

የቅንጅት አስፈላጊነት አያጠያይቅም ያሉት አቶ ምርጫው፤ እንደ ፖርቲዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብም ቅንጅት መፍጠር አለበት ብለዋል።

“ሰላማዊ ትግል አስፈላጊ ነው ያሉም ሲሆን፤ “ይህንን ስለመረጥን የሚወቅሱን አሉ፡፡ ለሰላማዊ ትግላችን ግን የሁሉም ትብብር ያስፈልገናል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፖርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ሀይማኖት በበኩላቸው፤ “የዚህ ቅንጅት ዋና አላማ የስልጣን ፍላጎት ሳይሆን ሀገር ከገባችበት ችግር ለማውጣት ማንኛውንም መሰዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ነው” ሲሉ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ገልጸዋል።

ትብብራችንን ሕጋዊ ቅርጽ አስይዘን አጠናቀናል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ የቅንጅቱን ስያሜ እና አርማም በዛው ዕለት ይፋ አድርገዋል።

ቅንጅቱ ከስያሜዉና ከፕሬዝዳንቱ ስያሜ በተጨማሪ ቅንጅቱ የሚጠቀምበትን ሎጎ ይፋ አድርጓል።

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት ፖርቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ የመረጡት የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አብርሀም ጌጡ በምስረታው ጉባኤ ላይ የቅንጅቱን አቋም መግለጫ አቅርበዋል።

በንግግራቸውም ጦርነት ለማስቆም፣ ኢትዮጵያ ከገባችበት የህልውና አደጋ ለመታገል፣ የኢኮኖሚ ውድቀትን ለመቅረፍ በአጠቃላይ ዜጋው በሀገሩ ተስፋ እንዲያደርግ ይህ ቅንጅት መመስረቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የፊያችን ግንቦት ወር ላይ ጠቅላላ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ስትሆን ምርጫ ቦርድ በመላው ሀገሪቱ ለማድረግ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዢው ብልጽግና ፓርቲን በቀጣዩ ምርጫ ላይ ለማሸነፍ ህብረት እና የጋራ ስምምነቶችን በማድረግ ላይ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *