በጃፖን ቶኪዮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየዉ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጲያ በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ያለ ምንም ወርቅ አጠናቃለች።
ኢትዮጲያ በዚህ መድረክ በታሪክ ከ34 አመት በኅላ አንድም ወርቅ ሳታገኝ ያጠናቀቀችበት የአለም ሻምፒዮና ሆኖ ተመዝግቧል።
በውድድሩ የመጨረሻ ቀናት በተደረገዉ የ5000 ሜትር የወንዶች ፍፃሜ ዉድድር ምን አልባት ወርቅ ይገኝበታል ተብሎ ቢጠበቅም ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ዉስጥ መግባት ሳትችል ቀርታለች።
ኢትዮጲያን የወከሉት አትሌት ሀጎስ ገብረ ሂወት እና አትሌት ቢኒያም መሀሪ ዉድድራቸዉን 5ኛ እና 13ኛ ደረጃን ይዘዉ አጠናቀዋል።
ኢትዮጲያ እስካሁን ባደረገቻቸዉ ስምንት የፍፃሜ ዉድድሮች ሁለት ብር እና ሁለት ነሀስ ስታገኝ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን ብቻ ሰብስባ በታሪኳ በእጅጉ ደካማ የሆነዉን የቶኪዮ አለም ሻምፒዮና ቆይታዋን ደምድማለች።
አሜሪካ በውድድሩ 16 የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በአንደኝነት ስታጠናቅቅ ኬንያ በሰባት ወርቅ እንዲሁም ካናዳ በሶስት ወርቅ ሜዳሊያ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ በሁለት ብር እና ሁለት ነሀስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም በ22ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በውድድሩ ከተሳተፉት አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው እና ለወርቅ ሜዳሊያ ተጠብቆ የነበረው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለአትሌቲክሱ ውጤት መጥፋት በቡድን አለመስራት አንዱ ምክንያት እንደነበር ገልጿል።
“በውጤቱ ህዝቡ እንደታመመ እኛም አሞናል “ ያለው አትሌቱ “ ውስጥ ስትሆን ደግሞ የበለጠ ነው የምትታመመው “ ሲል ገልጿል።
ለውጤት መጥፋቱ ምክንያት ያላቸውን የጠቀሰው አትሌት ሰለሞን ባረጋ “ እኛ በተወዳደርንበት የወንዶች 10,000 ሜትር ርቀት ውጤት የጠፋው አብረን ባለመስራታችን ነው “ ሲል አስረድቷል።
“ እኔ በሪሁ አረጋዊ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ ሶስታችንም ሶስት ሀገር ሆነን ነው የሄድነው “ የሚለው ሰለሞን “ አንተዋወቅ አያቀኝ አላቀው “ ሲል ተደምጧል።
“ ሶስት ሀገር ሆነን ኢትዮጵያን ወክለን መስለን ሮጥን“ ያለው አትሌቱ “ በምን እንተዋወቅ አልተነጋገርንም ውድድር ውስጥ ስንገባ አላወራንም ምን መሆን እንዳለበት አልተነጋገርንም ነበር “ ብሏል።
አክሎም “ አብረን ካልሰራን ሆቴል ለምን ገባን “ ሲል የጠየቀው አትሌት ሰለሞን “ በቂ ቁጥጥር እና ስልጣናም እንዳልነበረ “ ተናግሯል።
አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እንደ ተቋም ራሱን ማስከበር እንዳለበት የጠቆመው ሰለሞን ” አብሬ አልሰራም ፤ አሰልጣኝ አላክብርም አልሰለጥንም በሚል አትሌት ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት ሲል አሳስቧል።
ሀገርን የሚወከሰሉ ተተኪ አትሌቶች እያፈራን አለመሆኑን ያነሳው አትሌቱ “ ነገሮችን በፍጥነት ማስተካከል አለብን“ ሲልም ከኢትዮ ራነርስ ሚዲያ ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ወቅት ተናግሯል።
” ይህ የማይሆን ከሆነ እንኳን ወርቅ ሚኒማ የሚያሟላ አትሌት ለማግኝት ልንቸገር እንችላለን “ ሲልም አትሌቱ የግል አስተያየቱን ሰጥቷል።