የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር እንደገለጹት ጥያቄውን ለማስተናግድ የኤሌክትሪክ አቅርቦታችን አቅም ማሳደግ እንደሚጠበቅ ገልፀው ይሄን አሁን ባለው አቅም ማስተናገድ እንደማይቻል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ባለው ዝቅተኛ የታሪፍ ዋጋ እና የኃይል ኃብት በመሳብ 25 ኩባንያዎች የቢትኮይን ማዕድን ቁፋሮ ስራ የጀመሩ ሲሆን፣ 20 የሚሆኑ ኩባንያዎች ደግሞ ፈቃድ ለማግኘት በዝርዝር ተመዝግበው እየጠበቁ ናቸው።
ኩባንያው ገቢውን ለማስፋት በማሰብ፣ “ተጨማሪ ኃይል” ብሎ የሰየመውን ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለክሪፕቶ ማዕድን አውጪ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሬ መሸጥ ጀምሮ ነበር።
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኤሌክትሪክ ሽያጭ 75.4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 25.18 ቴራ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት ደንበኞች ለሽያጭ ቀርቧል ብለዋል።
ከአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሽያጭም 74.05 ቢሊየን ብር እንዲሁም 1.41 ቢሊየን ብር ደግሞ ከተጓዳኝ አገልግሎቶች መገኘቱንም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ኢንጅነር አሸብር ባልቻ በማብራሪያቸው እንዳሉት 60 በመቶ ለኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ 27 በመቶ ለዳታ ማይኒንግ፣ 6 በመቶ ለኢንዱስትሪዎች፣ 5 በመቶ ለኬንያ፣ 2 በመቶው ደግሞ ለጅቡቲ ተሽጧል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ከተሸጠ ሀይል 118 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ይታወሳል።
ታንዛኒያ ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ ሀይል የተሸጠላቸው ሀገራት ሲሆኑ ለሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከውኃ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑን ኢንጂነር አሸብር ገልጸዋል፡፡