አንጋፋዋ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
አምባሳደር ቆንጂት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርን በ1950ዎቹ በለጋ እድሜያቸው ተቀላቅለው ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት አገልግለዋል።
አምባሳደር ቆንጂት ከዮዲት እምሩ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደርም ናቸው።
አምባሳደሯ በኦቶዋ፣ ካይሮ፣ ቴል አቪቭና ቬይና በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በአፍሪካ ህብረትና በተባባሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሰርተዋል።
ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011ዓ.ም ደግሞ ኢጋድ በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይም ልዩ አማካሪ ነበሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአምባሳደር ቆንጂት ሕልፈትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ዲፕሎማቷን እንዳጣች እና ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መጽናናትን ተመኝቷል።
አምባሳደር ቆንጅት ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ባበረከቱት አስተዋጽኦ በ2019 በጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ የክብር ኒሻን ሽልማት ተብረክቶላቸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ የዲፕሎማቷን ሞት አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት ጽሁፍ “አምባሳደር ቆንጂት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ኢትዮጵያን በዲፕሎማትነት በማገልገል፣ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥለው ሁለተኛዋ ሴት የኢትዮጵያ አምባሳደር ናቸው። ለሕግ፣ ለአሠራር፣ ለፕሮቶኮል እና ለኢትዮጵያ ጥቅሞች በነበራቸው የጸና አቋም እናስታውሳቸዋለን። ከእርሳቸው በኋላ አያሌ ሴት ዲፕሎማቶች በመስኩ እንዲሠማሩ መንገዱን አስፍተዋል” ብለዋል።