የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፊታችን ግንቦት ሊካሄድ ስለታሰበው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት አካል የሆነው የምርጫ ምዝገባ ሂደት ላይ እየደረሱ ያሉ ተገቢ ያልሆኑ ተጽዕኖዎች እና ጣልቃ ገብነቶችን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
ቦርዱ በመግለጫው እንደጠቀሰው በክልል መንግሥታት እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ስር ባሉ አስፈጻሚዎች አማካኝነት ቤት ለቤት በመሄድ ” ተመዝገቡ ” የሚል ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ደርሼበታለሁ ብሏል።
የምርጫ ካርድ መውሰድን እንደ ግዴታ በመቁጠር ጫና መፍጠር፣ የመራጭነት ምዝገባን ከማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር ማያያዝ፣ እንዲሁም ” የመራጭነት ካርድ ካልወሰዳችሁ ደመወዛችሁ ይቆረጣል ” በማለት በሠራተኞች ላይ ተጽዕኖ የማሳደርና ከሥራ እንደሚያሰናብቱ በመግለጽ የማስፈራራት ድርጊቶች እየተፈጸሙ እንደሆነም ቦርዱ አስታውቋል።
ማንኛውም አካል በየቤቱ በመሄድ “ተመዝገቡ” ማለት ወይም በየመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞችን “ተመዝገቡ” ብሎ ማስገደድ እንደማይችል የገለጸው ቦርዱ፤ ” የመራጭነት ካርድ ካልወሰዳችሁ ደመወዝ ይቆረጣል ” ወይም ” አገልግሎት ይከለከላል ” ማለት ሕገ-ወጥ ድርጊት መሆኑንም አሳስቧል።
በመሆኑም ቦርዱ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትንና ተቋማትን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግና እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖ ባለባቸው የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ምርጫ እንዳይካሄድ እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም አስጠንቅቋል።
ዜጎች መምረጥ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው እንጂ ግዴታ አለመሆኑን ተገንዝበው በራሳቸው ፍላጎት ብቻ እንዲመዘገቡ ፤ ካልተመዘገቡም ደመወዝ የሚያስቆርጥ፣ ከስራ የሚያስወጣ ወይም የሚያስባርር አልያም አገልግሎት የሚያስከለክል እንዳልሆነ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 እንደሚካሄድ የሚጠበቅ ሲሆን በጸጥታ ስጋት ምክንያት ፓርቲዎች በሁሉም ክልሎች ተንቀሳቅሰው መስራት እንዳልቻሉ በመግለጽ ላይ ናቸው።