የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ መጠቀም መጀመሯን ተከትሎ አስገዳጅ ደረጃዎች ማዘጋጀቱን ገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ በሰጡት መግለጫ 79 አጠቃላይ ደረጃዎችን መዘጋጀታቸውን ገልጸው ከዚህ ውስጥ ሰባቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ደረጃዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ እና ከውጭ ለሚገቡ በነዳጅ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ደረጃዎች እንዳሏት የተናገሩት ዶክተር መሰረት በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ግን የሚመዘኑበት የጥራት ማስጠበቂያ ደረጃ እንዳልነበራት አክለዋል፡፡
አዲሱ ደረጃ የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ ሲገጣጠሙ ሊሟሉ የሚገቡ መስፈርቶችን የያዘ እንደሆነም ተገልጿል።
በኢንስቲትዩቱ የደረጃዎች ዝግጅት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ይልማ መንግስቱ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ጥራት ለማስጠበቅ የወጣው ደረጃ በሶማሊ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ መጠቀም በመጀመሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ አዲሱ ደረጃ የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚገባቸው የሚያስረዳ ነው፡፡
በዚህ የጥራት ደረጃ ላይ ከተጠቀሱት መስፈርቶች መካከል የተሸከርካሪዎች ነዳጅ ማጠራቀሚያ፣ እንደ ፍሬን ያሉ የደህንነት ማስጠበቂያ ምርቶች የሚገኙበት ጥራት፣ የተሽከርካሪው አጠቃላይ አካል እና የኤሌክትሮ መካኒካል መግባቢያ መሳሪያዎች ጥራት ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል፡፡
ከትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተዘጋጅቷል የተባለው አዲሱ ደረጃ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ በጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ምን አይነት መስፈርት ማሟላት አለባቸው የሚለውን የሚወስን እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከዚህ በፊት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ነገር ግን ሞተራቸውን ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መቀየር የሚያስችል የጥራት ማስጠበቂያ ደረጃ ገና አልተዘጋጀም፡፡
ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ሞተር ለመቀየር የራሱ የሆነ ጥናት እና ጊዜ እንደሚፈልግ የገለጹት ዳይሬክተሩ የአንድን ተሽከርካሪ ሞተር ለመቀየር ከሻንሲ ቁጥር አሰጣጥ ጀምሮ የባትሪ ቦታ መፈለግ፣ የባትሪ አቅምን መለየት ፣ ሞተራቸውን መቀየር የሚችሉት ተሽከርካሪዎችን መለየት እና ሌሎች ስራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚገባም አክለዋል፡፡
በቀጣይ አዲስ የተሽከርካሪ ሞተር መቀየር የሚያስችሉ ደረጃዎች ሊዘጋጁ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ሚንስቴር ከመስከረም 30፣ 2018 ጀምሮ “በተፈጥሮ ጋዝ” የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና ፈሳሽ ጭነት እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ መፍቀዱ ይታወሳል።
ሚንስቴሩ ውሳኔውን ያስተላለፈው ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ መሆኑን በወቅቱ ገልጾም ነበር።
እንዲሁም ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ በሶማሊ ክልል ካሉብ የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ባስመረቁበት ወቅት ነዳጅ የሚጠቀሙ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ከመስከረም 22፣ ጀምሮ መከልከሉን ተናግረው ነበር።