ኢትዮጵያ ግብጽን በስጋትነት እንደማትመለከታት ገለጸች

ግብፅ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እያደረገች ያለችውን ጫና ኢትዮጵያ በስጋት አንደማትመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ሳምንታዊ መግለጫ ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ለኢትዮጵያ ስጋት አይሆንም ሲል ተናግሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር  ነቢያት ጌታቸው የግብፅ አካሄድ ስጋት የማይሆነው ከዚህ ቀደምም የነበረ ስለሆነ ነው ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡ ምርቃት መቃረቡን ያስታወሱት አምባሳደር  ነቢያት ጌታቸው የቅኝ ግዛት እሳቤዎች ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።

በለፉት 14 ዓመታት በመላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ከፍተኛ መሰናክሎችን አልፎ ህዳሴ ግድቡ የመመረቅያው ዋዜማ ላይ እንገኛለን ያሉት አምባሳደሩ ምርቃቱንም ኢትዮጵያዊያን  እና የኢትዮጵያን በጎ የሚመኙ አብረውን የሚያከብሩት  ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለምርቃቱ በስም ያልዘረዘሯቸው እንግዶች እንደተጋበዙ የተናገሩት ነብያት ጌታቸው ጊዜው ሲደርስ እነማን እንደሚገኙ የምናየው ይሆናል ብለዋል፡፡

ግድቡ ከጥንስሱ ጀምሮ የውጭ ሃይላትን ድጋፍ በገንዘብም፣ በፖለቲካም፣ በግብዓትም ታሳቢ አድርጎ የተጀመረ አይደለም፤ እኛ እና እኛን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ነው  ሰሉ አብራርተዋል፡፡

ስለዚም የምርቃቱን ድል በምናበስርበት ቀን ከጎናችን የሚቆሙ ወዳጆቻችን ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን፤ በዋነኝት ግን የእኛ የኢትዮጵያዊያን ጽናት ውጤት ያመጣበት ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል አምባሳደር  ነቢያት ጌታቸው፡፡

ኢትዮጵያ የኢነርጂ ዲፕሎማሲ ላይ እየሰራች ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት የጋራ ሃብትን በጋራ ማልማት እና  መጠቀም ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አላት ሲሉ አስረድተዋል።

ግድቡም አፍሪካዊያን በራሳቸው አቅም ሃብታቸውን ማልማት እና መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የወጣበት የህዳሴው ግድብ መስከረም ወር ላይ ተመርቆ 5200 ሜጋዋት ሀይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሏል።

ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ምረቃ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙ ሀገራት መካከል ሲሆኑ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ግብዣውን በይፋ ከተቀበሉ ሀገራት መካከል አንዱ ናቸው።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ሀይል አቅም አሁን ካለበት በዕጥፍ እንደሚያሳድገው ተገልጿል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ሀይል በመሸጥ ላይ ስትሆን ለሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በ2024/25 ዓመት ለጎረቤት ሀገራት ከተሸጠ ሀይል 120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *