ሴኔጋላዊው አል ሀጂ ዲዮፍ የዋናው ስፖርት ኩባንያ አምባሳደር ሆነ

የሴኔጋሉ የእግር ኳስ ኮኮብ አልሀጂ ዲዩፍ በኢትዮጵያ ላለ አንድ የስፖርት ትጥቅ አልባሳት አምራች ኩባንያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል።

ስምምነቱ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን “ከአፍሪካ ምርጡ ትጥቅ አምራች ጋር ስምምነት ፈፅሜያለሁ “ ብሏል ዲዩፍ።

ሴኔጋላዊው የቀድሞ ታሪካዊ ተጨዋች ኤል ሀጂ ዲዩፍ የኢትዮጵያው ትጥቅ አምራች ብራንድ ዋናው አምባሳደር በመሆን መሾሙን ኩባንያው ገልጿል።

ታሪካዊው ተጫዋች የዋናው ስፖርት አልባሳት በሚመረትበት አዲስ አበባ ሀብቴ ጋርመንት እና ህትመትን ከጎበኘ በኋላ ስምምነት ፈፅሟል።

“ ከአፍሪካ ምርጡ ትጥቅ አምራች ጋር ስምምነት ፈፅሜያለሁ “ ሲል ዲዩፍ ከጉብኝቱ በኋላ ተናግሯል።

አክሎም  “በቀጣይ ከትልልቅ ታሪካዊ ተጫዋቾች ጄጄ ኦኮቻ ፣ ኑዋንኩ ካኑ ፣ አዲባየር እና ካሊዱ ፋዲጋን በማምጣት ዋናውን በአለም ገናነቱን እናሳየለን ” ብሏል።

“ በቀኝ ግዛት ባልተገዛችው ብቸኛዋ ሀገር 🇪ኢትዮጵያ በመምጣቴ ደስታ እና ኩራት ተሰምቶኛል” ሲልም ዲዩፍ ተናግሯል።

ዲዩፍ ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽም “ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ጥሩ እና በአፍሪካ ምርጥ ይሆናል ” ሲል ገልጿል።

” ለኢትዮጵያ ጥሩ ነገር የአፍሪካ ዋንጫን በ 2029 የማስተናገድ እድል አላት ይህ እንዲሳካ በጋራ እንሰራለን ኢትዮጵያ ማስተናገድ ይገባታል“ ብሏል።

“ የኢትዮጵያ ህዝብ ኳስ እንደሚወድ አውቃለሁ” ያለው ዲዩፍ ይህ እንዲሆን የሚቻለውን ያህል ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

የዋናው ስፖርት ትጥቅ አምራች ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሀብተስላሴ ገ/ ክርስቶስ በበኩላቸው “ ለዲዩፍ ጥያቄውን ስናቀርብ ሁለቴ አላሰብም ሀሳባችንን ወዶታል ፤ ዋናው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያን ከአለም ተፎካካሪ ብራንድ ለማድረግ ስራዎችን በጋራ እንሰራለን ” ብለዋል።

ዋናው ስፖርት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለቦች የስፖርት ትጥቅ በማቅረብ ላይ ሲሆን ለሌሎች አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የስፖርት አልባሳትን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት አቅም እንዳላት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤውን ባሳለፍነው ጥቅምት በአዲስ ባደረገበት ወቅት አስታውቃለች።

የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ በበኩላቸው
ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ካፍ ከኮሚቴው ጋር እንደሚመክርበት ገልዋጸል።

ኢትዮጵያ የካፍን ደረጃ የሚመጥኑ ስታዲየሞች የሌላት በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎችን ከሀገሩ ዉጪ ለመጫወት ተገዷል።

የዉድድሩ አዘጋጅ ሀገራት ቢያንስ ስድስት ስታዲየሞችን እንዲያዘጋጁ ካፍ ቢያዝም ኢትዮጵያ እስካሁን የካፍን ደረጃ ያሟላ ስታዲየም የሌላት ሲሆን ውድድሩን ለማዘጋጀት እያደረገች ስላለው ዝግጅት የተባለ ነገር የለም፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች አንድ ስታዲየም ያላት ቢህንም ከዚህ ውስጥ አንዱም የካፍን ደረጃ የማያሟላ ሲሆን በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው እና 62 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች መጠናቀቅ አልቻለም፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም እስካሁን ዋንጫውን አንድ ጊዜ ብቻ ማሸነፍ ችላለች፡፡

በ1962 የአፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጀችው ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ተጫውታ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ችላለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *