ሀገራዊ ፓርቲ ለመሆን በስድስት ክልሎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብን የሚያስገድደዉ አዋጅ ፀድቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ጉባኤ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል።
አዋጁ ከነባሩ አዋጁ 1162/2011ዉስጥ የነበሩ 26 አንቀጾችን ያሻሻለ ሆኖ የቀረበ ነዉ ተብሏል።
አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመወዳደር ከ 6 ክልሎች የ60 በመቶ ድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብን የሚያስገድድ አንቀፅ ይገኝበታል።
ከዚህ ቀደም ሀገራዊ ፓርቲ ለመሆን የአራት ክልሎች የድጋፍ ፊርማ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህንን አንቀፅ ለማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት የተጨመሩ ክልሎች መኖራቸዉን ታሳቢ አድርጎ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል።
በዚህ መሰረት ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት በስድስት ክልሎች የድርጅት አባል ማፍራት እንዳለባቸዉ የሚያደርግ ነዉ።
አንድ የምክር ቤት አባል የሀገራዊ ፓርቲ ምስረታን በየክልሎች የድጋፍ ማሰባሰብ ሂደቱን በተመለከተ ያን ለማድረግ አሁን አመቺ ሁኔታ አለ ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ሌላኛዉ የምክር ቤት አባል በአዋጁ ረቂቅ ላይ ዉይይት በተደረጉባቸዉ መድረኮች ላይ መገኘታቸው ገልፀዉ በመድረኮቹ ተነስተዉ የነበሩ የሀሳብ ግብአቶችን የቀረበዉ ማሻሻያ እንዳላካተተ አንስተዋል።
የምክር ቤት አባሉ አያይዘውም የስድስት ክልሎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የሚለዉ ብዙም የሚያስኬድ አይመስለኝም ብለዋል።
ለምሳሌም ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ዉጪ በሁሉም ክልሎች አንድ የፓለቲካ ፓርቲ ቢወዳደር ትርጉም የለዉም 50 በላይ መቀመጫ ማግኘት አይችልም ሲሉ ገልፀዋል።
ከ547 ወንበር ወደ 316 ወንበር ያለዉ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ነዉ። ስለዚህ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ተወዳድሮ ያሸነፈ ፓርቲ መንግስት መሆን ይችላል ሲሉ ገልፀዋል።
የምክር ቤት አባሉ መታየት ያለበት የክልሎች ብዛት ሳይሆን በፓርላማ ወንበር ቁጥር ባሉ የምርጫ ክልል ዉስጥ መወዳደር የቻለ ፓርቲ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ መቀጠል ይችላል የሚለዉ ታሳቢ ቢደረግ ብለዋል።
ሌላዉ ከምክር ቤት አባላት የብሄር ፓርቲዎችን ከማስቀረት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ሆነዉ እንዲሰባሰብ ከማድረግ አንፃር አዋጁ ምን እንደያዘ ተጠይቋል።
የዲሞክራሲ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እዉነቱ አለነ ይህንን አስመልክቶ ይህንን በፓርቲዎች ፍላጎት እንጂ በአዋጅ ይህንን ማድረግ የማይቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1394/2017 አድርጎ በሁለት ተቃውሞ፤ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ የስታርት አፕ እና የፌደራል ገቢ ግብር ረቂቅ አዋጆችን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።