የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳድር ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የዓለማችን ሀገራት ላይ አዲስ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።
አዲሱ ታሪፍ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ጠቅላላ ምርት ላይ የ35 በመቶ ገቢ እንዲቀንስ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር የአሜሪካ አስተዳደር ፖሊሲ ከሀገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ 35 በመቶ የሚሆነውን የሚነካ ነው ብለዋል።
በዚህ ምክንያትም ከአሜሪካ ባለፈ አማራጭ የውጭ ገበያዎችን በመመልከት ላይ መሆናቸውንም ሻፊ ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያን ቡና ወደ ሩቅ ምስራቅ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የማስፋት እቅድ ተይዟል ተብሏል።
በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥም 20 አዳዲስ የቡና ወጪ ንግድ መዳረሻዎችን የመክፈት እቅድ እንደተያዘም ተገልጿል።
እንዲሁም ዋነኛ የኢትዮጵያ ቡና ገዢ ወደ ሆኑት ቻይና፣ ጃፓን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጀርመን እና ጣሊያን ጋር ግኑኝነትን በማጠናከር ተጨማሪ ቡና የመሸጥ እቅድም ተይዟል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የቡና ዘርፉን የሚጎዳ የትኛውንም ዓይነት እርምጃ አይቀበልም ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።
ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከችው ቡና 2.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገልጿል።
በአጠቃላይ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን የወርቅ እና ቡና ንግድ ከግማሽ በመቶ በላይ ሸፍነዋል ተብሏል።