አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በነጩ ቤተ-መንግሥት ተገናኝተው ተወያይተዋል ።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ ጋር በነጩ ቤተ-መንግሥት ተገናኝተው ተወያይተዋል።
አምባሳደር ብናልፍ ነጩ ቤተ-መንግሥት ሲደርሱ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚያንጸባርቅ ዲፕሎማሲያዊ አቀባበል እንደተደረገላቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
ይህ የመጀመሪያ ግንኙነት በቀጣይ ጊዜያት ለሚደረጉ ውይይቶች መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል የተባለም ሲሆን፤ አምባሳደሩ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ተገናኝተው ስላደረጉት ውይይት በይፋ የተገለጸ ነገር የለም
ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ በሁለቱ አገራት መካከል እንደ ሰላም፣ ጸጥታና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ጠንካራ አጋርነት ከመፍጠር አንጻር ያሉ ዕድሎችም ሰፊ መሆኑ ተመላክቷል።
አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም በውይይቱ ወቅት የተገኙትን ስቴት ሴክሬተሪ ማርኮ ሩቢዮ ጋርም መገናኘታቸው ተነግሯል።
አምባሳደር ብናልፍ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ ነበር በአሜሪካ የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለን ተክተው የተሾሙት።
አምባሳደር ስለሺ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ሹመታቸውን ለመልቀቅ የመልቀቂያ ካስገቡ በኋላ በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሌንጮ ባቲ ይተኳቸዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡
ይሁንና አሜሪካ የአምባሳደር ሌኝጮ ባቲን ሹመት መቃወሟን ተከትሎ ብናልፍ አንዷለም በዋሸንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡
አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በሳዑዲ አረቢያ አምባሳደርነት የተሾሙት በ2013 አጋማሽ ነበር።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በአማካሪነት፣ በኋላ ደግሞ በአምባሳደርነት እያገለገሉ የሚገኙት ሌንጮ ባቲ፣ የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንደኛው ክንፍ አመራር ነበሩ።
አምባሳደር ሌንጮ በአሜሪካ ለዓመታት የመንግስት ተቃዋሚ ሆነው የኖሩ ሲሆን ከጾታዊ ትንኮሳ ጋር የተያያዘ ክስ ተመስርቶባቸው ነበር በሚል ወደ ዋሸንግተን ሳይጓዙ ቀርተዋል፡፡