አሜሪካ ፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም እቅዳቸውን እንዲያሳውቁ ጠየቀች

አሜሪካ ዛሬ አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲዋ በኩል ለፌዴራል መንግሥት እና ለታጣቂዎች መልዕክት አስተላልፋለች።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት በመላው ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት የዳረጉ ግጭቶች ሰላማዊና ትክክለኛ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አምባሳደሩ፥ ለታጣቂ ኃይሎች እና ለፌደራል መንግስት ባስተላለፉት መልዕክት ህዝብን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል።

” ጦርነቱን ማቆም፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መርዳት እና ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው ” ሲሉ አስገንዝበዋል።

” በትጥቅ ትግል ስም የሚፈጸሙ ህገወጥ እና የኃይል እርምጃዎች ሊቆሙ ይገባል ” ብለዋል።

አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በመልዕክታቸው ለፋኖ ፣ ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) እና ለፌደራል መንግስት የተናጠል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህም በአማራ ክልል ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ጋር የትጥቅ ትግል እያደረገ ላለው ፋኖ ተጨባጭ የሆነ እና ሰላማዊ የሆነ ዓላማ/ግብ ይዞ እንዲመጣ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) ደግሞ በኦሮሚያ ያለውን ግጭት ለማስቆም ድርድሩን እንዲቀጥል እንዲሁም የፌደራል መንግስት በራሱ ዜጎች ላይ የሚያደርገውን የድሮን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆምና ረጅም እርምጃ ወደ ለሰላም በመምጣት መፍትሄዎችን እንዲያመቻች ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደሩ በመልዕክታቸው ማጠናቀቂያ ” ሰላምና መረጋጋት የምንመርጥበት ጊዜ አሁን ነው ” ብለዋል።

በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ከአራት ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ሲሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በግጭት እና ጦርነት ምክንያት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *