በሱዳን ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ወደ ሀገሪቱ የምትልከው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን በ80 ከመቶ ያህል መቀነሱን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል፡፡
የተቋሙ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ የሱዳን የሃይል መሰረተ ልማት በጦርነቱ በመጎዳቱ የታቀደውን ያህል መጠን ሀይል መላክ አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡
አቶ ሞገስ መኮንን እንዳሉት “ከሱዳን ጋር የተደረገው ስምምነት እስከ 100 ሜጋዋት ድረስ ለመላክ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በመጠን ደረጃ በጣም ቀንሷል፡፡ ከ10 እስከ 20 ሜጋዋት ድረስ ነው እየላክን ያለነው፡፡ ዝቅ ሲል እስከ 10 ሜጋዋት፣ ከፍ ሲል ደግሞ እስከ 20 ሜጋዋት ይሆናል የምንልከው፡፡
ይህ የሱዳን የኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተልማት በጦርነት በመጎዳቱ የመጣ ችግር ነው፡፡ ግጭቱ በጣም ከፍተኛ በሆነ መንገድ መሰረተልማቱን ጎድቶታል ብለዋል፡፡”
ከሁለት ዓመት በፊት ጦርነቱ እንደተቀሰቀሰ፣ መጀመሪያ ላይ 100 ሜጋዋት ሙሉውን ይወስዱ ነበር፡፡ ጦርነቱ እየተባባሰ ሲሔድ ግን ሃይል የመውሰድ ፍላጎታቸው እየቀነሰ መጣ፡፡ ችግሩ በአንዴ የመጣ አይደለም፣ በሒደት የመጣ ነው ” ብለዋል አቶ ሞገስ።
ይኸው ጦርነት በሚላከው የሃይል መጠን ላይ ብቻ ሳይሆን ሱዳን የተጠቀመችውን የኤሌክትሪክ ሀይል መክፈል እንዳልቻለችም አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡
“ክፍያዎች ላይም አንዳንድ መዘግየቶች አሉ፣ መጠኑን ለመግለፅ ባልፈልግም፣ ከሱዳን ያልተሰበሰበ ሒሳብ አለን፡፡ ወደፊት መከፈል አለበት፣ መንግስትም ጣልቃ ይገባበታል ብለን እናስባለን፡፡ ሱዳኖቹ፣ አሁን ያለውን ችግራቸውን መፍታት ከቻሉ፣ ወደፊት እንደሚከፍሉ ይናገራሉ፡፡ እኛ ደግሞ እንደ መልካም ጎረቤት፣ ይህን ተቋቁመን እየላክን ነው፡፡ አለምአቀፍ ስምምነት ስላለ፣ በማንኛውም ሰዓት ለማስከፈል የሚከለክል ነገር የለም፡፡ ሀገሪቱ ሰላም እስክታገኝ ድረስ መላካችንን እንቀጥላለን” ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን በተጨማሪ ለጅቡቲ እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል በመላክ ላይ ስትሆን ከጥቂት ወራት በኋላ ለታንዛንያ ሃይል ማቅረብ እንደምትጀምርም አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡
“ ከታንዛኒያ ጋር ድንበር ስለማንጋራ፣ በኬንያ በኩል ነው ለሀገሪቱ ሃይል የምንልከው፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ 2000 ሜጋዋት ኃይል የሚሸከም የማስተላለፊያ መስመር አለ፣ ከኬንያ ወደ ታንዛኒያ የተዘረጋ ደግሞ አለ፡፡ ስዚህም ጉዳዩ የሶስትዮሽ ስምምነት ያስፈልገው ስለነበረ፣ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ከዛ በኋላ፣ ከኬንያ ጋር የሃይል ማስተላለፊያ ስምምነት፣ ከታንዛኒያ ጋር ደግሞ የሀይል ግዢ ስምምነት በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ተፈርሟል፡፡ በመጪው ሚያዝያ ወደ ታንዛኒያ 100 ሜጋዋት የኤሌአክትሪክ ሃይል መላክ ይጀመራል ” ሲሉ አሳውቀዋል።
ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመግዛት፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊላንድም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል የተባለ ሲሆን በተለይም ለደቡብ ሱዳን ለመላክ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቁን የሀይል ማመንጫ በአባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ስትሆን ከስድስት ወራት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሏል።