የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የ32 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ድጋፍ አደረገ

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ ለስድሰት የልማት ፕሮጀክቶች የሚውል የ32 ቢሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ለስድሰት ዋና ዋና የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል የ240 ሚሊየን ዩሮ ወይም የ32.3 ቢሊየን ብር የልማት ድጋፍ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን አስተዳደርና አካታችነትን በማሻሻል መረጋጋትን ማስፈን የሚለው ይገኝበታል።

በተጨማሪም በግጭት የተጉዱ የጤና ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለመመለስና እንዲሁም ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል፡፡

የስራ ዕድል የሚፈጥሩ የግብርና ስራዎችን፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመጠቀም የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ልማትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማምጣት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ደግሞ ሌሎቹ የድጋፍ ስምምነቱ ፕሮጀክቶች አካል መሆናቸው ተጠቁሟል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት ድጋፉ የግሉ ዘርፍን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲጨምር ለማገዝ፣ የታክስና ጉምሩክ ስርዓቱን ለማዘመን፣ የግብርና፣ጤናና ትምህርት አገልግሎትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊያ ኢሜስበርገር በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት የኢትጵያን ዘላቂ ልማት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው ይህ የልማት ድጋፍ ስምምነት የጋራ እሴቶቻችንና የወደፊቱ የእድገት ግቦች ስኬታማነት መገለጫም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

የልማት ድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ሀላፊ አምባሳደር ሶፊያ መፈረማቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የልማት እና ሰብዓዊ ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል ዋነኛው ሲሆን በ2023 ዓመት ብቻ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ድጋፍ አድርጎ ነበር፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *