የመንግስት እና የግል ተቋማት ከሚሰጧቸው የተለያዩ አገልግሎቶች “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” የሚሆን ገቢ እንዲሰበስቡ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ባሳለፍነው ሳምንት ለፓርላማ መቅረቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሳይወስን ገንዘብ ለመሰብሰብ አዲስ ረቂቅ ማስተዋወቁ ማንም አይጠይቀኝም ከሚል የመነጨ ነው ብሏል፡፡
መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወስን በፓርላማ የፀደቀውን አዋጅ ሳያስተገብር ከሰራተኛው ላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ አዲስ ረቂቅ ማስተዋወቁ ማንም አይጠይቀኝም ከሚል የመነጨ ነውም ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን እንደ አዲስ እንዲቋቋም የታሰበው የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ለተቀጣሪ ሰራተኞች ራሱን የቻለ አደጋ ነው ብሎታል።
ከሳምንት በፊት በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ የቀረበው የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ገቢን እሰበስብበታለሁ ያለው አማራጭ በሀገሪቱ የሚገኙ የግልም ሆነ የመንግስት ተቀጣሪ ሰራተኞችን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን ገልጿል።
የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ኮሚሽኑን ማቋቋም ክፋት ባይኖረውም በኑሮ ውድነትና ተያያዥ ችግሮች አደጋ ውስጥ ከሚገኝ ሰራተኛ ገቢ ለመቁረጥ ማሰብ ግን የመንግስትን ማን አለብኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ለአራዳ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ረቂቅ አዋጁ ለምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ ከመቅረቡ አስቀድሞ ሰራተኛው ሀሳብ ሊሰጥበት ሲገባ በደፈናው ደመወዝህ ይቆረጣል ብሎ በአዋጅ ማካተት ተገቢነት የሌለው አሰራር መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስት በ2011 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ የወጣውን የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ማስተግበሪያ አዋጅ እስከአሁን አላስፈፀመም።
በተጨማሪም የሰራተኞች የተጋነነ የደመወዝ ታክስ ክፍያን እንዲቀንስ ቢጠየቅም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ብሏል ኢሠማኮ።
ይህ በሆነበት ሁኔታ ግን በአስቸኳይ አዲስ አዋጅ አፀድቃለሁ ብሎ መነሳት የተቀጣሪ ሰራተኞችን መብት መጋፋትና ራሱ መንግስት ላወጣው ህግ ተገዥ አለመሆኑን አመላካች መሆኑን ነው የተናገሩት።
በሀገሪቱ በተከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ብሎም በዋጋ መናር ምክንያት ሰራተኞች በልተው ማደር የማይችሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል የሚለው ኢሠማኮ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከሰራተኞች የተጣራ የወር ገቢ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ ለአደጋ ጊዜ ብሎ ለመቁረጥ ማሰብ ለሰራተኛው ተጨማሪ አደጋ መደቀን ነውም ብሏል።
የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ገቢ አሰባሰብን በተመለከተ 15 ዝርዝር ጉዳዮች የሰፈሩ ሲሆን ከደመወዝ ላይ ከሚቆረጠው ገንዘብ በተጨማሪ እንደየሁኔታው ሰራተኞች በመንግስትም ሆነ በግል ጉዳይ በሚያከናውኗቸው ተግባራት ሊቆረጥባቸው የሚችል ገንዘብ እንደሚኖር ረቂቁ ያሳያል።