የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከየካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ በተለያዩ የብድር ዓይነቶች ላይ ጭማሪ ማድረጉን አስታዉቋል።
ይህ ጭማሪ የመጣው መንግስት የፋይናንስ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት አካል እንደሆነ ባንኩ ገልጿል።
በተደረገው ማስተካከያ መሰረት፣ የግብርና ብድሮች እስከ 15.5%፣ የንግድ ብድሮች እስከ 18%፣ የወጪ ንግድ ብድሮች እስከ 14%፣ የግል ብድሮች ደግሞ እስከ 15% ጭማሪ አሳይተዋል።
ይሁንና ባንኩ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ወይም ኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ብድሮች የወለድ ምጣኔው በነበረበት በ12 በመቶ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የውጭ ምንዛሬ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ሰራተኞች የግል ብድሮች በስምምነቱ ውል ላይ በመመስረት ከ11 በመቶ እስከ 13 በመቶ የሚደርስ ሲሆን፣ ለየት ያለ ከፍተኛ ዋጋ ላላቸው ደንበኞች ሰራተኞች የግል ብድሮች በ12 በመቶ እንደነበረው እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ 1.54 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ከቀናት በፊት መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ 1.54 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ እስከ የካቲት 16 ቀን 2017 ድረስ የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ ብዛት ከ350 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱም ተጠቅሷል።
በዚህም የባንኩ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.54 ትሪሊዮን ብር መሻገሩን ተጠቁሟል።
አጠቃላይ በባንኩ ከተፈጸሙ የገንዘብ ግብይቶች 84.5 በመቶ የሚሆነው በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የተፈጸሙ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን በዘንድሮው የበጀት ዓመት ጠቅላላ የብድር መጠን ወደ 1 ነጥብ 35 ትሪሊየን ብር ማደጉ ተነግሯል።
ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በፊት ባንኮች ለደንበኞቻው በሚሰጧቸው የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ተመን ያስቀምጥ የነበረ ቢሆንም ካሳለፍነው ሐምሌ ወር ጀምሮ ግን ይህን ተመን በማንሳት ባንኮች በራሳቸው እንዲወስኑ ፈቅዷል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ውሳኔን ተከትሎ ሁሉም የኢትዮጵያ ባንኮች ያዋጠናል ያሉትን የወለድ ምጣኔ ከ17 እስከ 22 በመቶ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ 29 ባንኮች ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ለዓመታ ለውጭ ባንኮች በሯን ዘግታ የቆየች ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት ይህን እገዳ ማንሳቷን ተከትሎ የአፍሪካ እና አውሮፓ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ባንኮች የበለጠ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ውህደት ለመፈጸም ውይይት በማድረግ ላይ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ባንኮች እንዲዋሃዱ እና ለውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስቧል፡፡