400 ያህል የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ የጥሪ ማዕከል ሠራተኞች “አይሶን ኤክስፔሪያንስ” የተሰኘ ወኪል ድርጅት ይፈጸምብናል ባሉት የአስተዳደር በደል ሳቢያ ላለፉት 2 ቀናት የሥራ ማቆም አድማ ላይ መሆናቸውን ዋዜማ ዘግቧል።
ሠራተኞቹ በዋናነት የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉት፤ በወኪል ድርጅቱ በኩል የሚከፈላቸው ደመወዝ ዝቅተኛ በመሆኑ እንደሆነ ታውቋል።
ወኪል ድርጅቱ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሠራተኞችን በተጠና መልኩ ከሥራ እንዲሰናበቱ እያደረገ እንደሆነና ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ብቻ 80 ያህል ሠራተኞችን ሕጋዊነቱን ባልተከተለ መንገድ እንዳሰናበተ ተነግሯል ።
ተመሳሳይ የሥራ ዓይነት ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ ቋንቋንና ማንነትን መሠረት ያደረገ ሕገወጥ የደመወዝ ልዩነትና አድሎ እንዳለና ድርጅቱ ችግሩን እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ተጠይቆ ሊያስተካክል እንዳልቻለ የድርጅቱ ሰራተኛ ማኅበር አስታውቋል ።
የድርጅቱ እህት ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋርነት ለኢትዮጵያ በሚል ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ላይ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ህጋዊ ፍቃድ ከተቀበለ ከአንድ ዓመት በኋላ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ሳፋሪኮም ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕን ያካተተ ነው።
ኢትዮጵያ ለውጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ በሯን መክፈቷን ተከትሎ ነበር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቴሌኮም አገልግሎት ነሀሴ 2014 ዓ.ም ላይ በድሬዳዋ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ለውጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ በሯን መክፈቷን ተከትሎ ነበር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡
ድርጅቱ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለ50 በመቶ ህዝብ እንዲሁም በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ደግሞ 98 በመቶ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የቴሌኮም አገልግሎት የመስጠት እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እንዳስታወቀው በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለኔትወርክ ማስፋፊያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድቤያለሁ ብሏል፡፡
ተቋሙ አክሎም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችበተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ 5 ሺህ አዳዲስ የኔትወርክ ማማዎችን እንደሚተክልም አስታውቋል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት የኔትወርክ አገልግሎቱን ለደንበኞቹ እየሰጠ መሆኑን ያሳወቀው ሳፋሪ ኮም ቀስ በቀስ የራሱን የኔትወርክ መስመሮች እየገነባ እንደሆነም ገልጿል፡፡
አሁን ላይ ድርጅቱ ከ2 ሺህ 500 በላይ የኔትወርክ ማማዎች አገልግሎት እየሰጠሁ ነው የሚለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 500 ያህሉ ራሴ የገነባኋቸው ናቸውም ብሏል፡፡