የኢትዮጵያ ውጭ እዳ መጠን ወደ 31 ቢሊዮን ዶላር አሻቀበ

የአገሪቱ የውጭ ዕዳ መጠን በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ከነበረበት 28.8 ቢሊዮን ዶላር ወደ 31 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን የገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው የሩብ ዓመት አጠቃላይ የመንግሥት የዕዳ ሰነድ አመላክቷል።

ለዚህ እንደምክንያት የተጠቀሰዉ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተግባራዊ መደረጉና በተጠቀሱት ሦስት ወራት ውስጥ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጅት (IMF) እና ዓለም ባንክ በድምሩ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ብድር የተለቀቀለት በመሆኑ ነዉ ተብሏል።

የዕዳ ሰነዱ እንደሚያሳየዉ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ከመደረጉ አንድ ወር በፊት ማለትም በሰኔ 2016 ዓ.ም. የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በገንዘብ ሲሰላ 207 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን በ2017 ዓ.ም. መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል።

የአገሪቱ ጂዲፒ ሲተመን ያሽቆለቆበት ምክንያትም ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ በመደረጉ እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል።

በዚህና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. የአገሪቱን ጂዲፒ 32.9 በመቶ ይዞ የነበረው አጠቃላይ የመንግሥት የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ (Public Debt) በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. ወደ 50.3 በመቶ ማሻቀብ የሪፖርተር ዘገባ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ካለባት አጠቃላይ ብድር መጠን ላይ ግማሽ ያህሉ ከቻይና የተገኘ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ዓለም ባንክ፣ አይኤምኤፍ እና ሌሎች ሀገራት ናቸው።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ከታማኝ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር መክፈሏን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በጦርነት፣ በኮሮና ቫይረስ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከተጎዳባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን አበዳሪ ሀገራት የብድር መክፈያ ጊዜ ላይ ሽግሽግ እንዲያደርጉም እየጠየቀች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የውጪ ንግድን ለማሳደግ በሚል የብርን የመግዛት አቅም በ100 ፐርሰንት በላይ ያዳከመች ሲሆን አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ145 ገደማ እየተመነዘረ ይገኛል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *