ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ የሌላቸው ድርጅቶች መኪና ወደ ሀገር ውስጥ እንዳያስገቡ ከለከለች

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያ ለመቀየር ጥናት እየተደረገ  መሆኑን የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወርቁ ደስታ እንዳሉት  “በሁለተኛው ምዕራፍ እየተከናወነ ባለው የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት በመኪና ማቆሚያዎች የኃይል መሙያ እየተሠራ ነው ” ብለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዴዔታ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው “ከዚህ በኃላ የተሽከርካሪ አስመጪና የሚገጣጥሙ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ሳይተክሉ በሥራ ላይ መሰማራት አይችሉም ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከ400 በላይ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እያስመጡና እየገጣጠሙ ነው የተባለ ሲሆን ሁሉም አስመጪዎች እና ገጣጣሚዎች የኃይል መሙያ እንዳላቸውም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከአንድ ሳምንት በፊት  ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሃይል መሙያ ማሽን (ቻርጀር) መትከል የሚፈቅድ መመሪያ ማዘጋጀቷ ይታወሳል።

በዚህ መመሪያ መሰረትም በመንገዶች ግራና ቀኝ በየ50 ኪሎሜትር ልዩነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መሙላት የሚችል ፈጣን ቻርጀር ጣቢያ ማቋቋም ይፈቅዳል፡፡

ይሁንና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሃይል ማቅረብ የሚፈልጉ ተቋማት ከነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ፈቃድ በመውሰድ እንዳለባቸው በመመሪያው ላይ ተጠቅሷል።

በተለያዩ ተቋማት የሚተከሉ የኤሌክትሪክ ሃይል መሙያዎች ከባለስልጣኑ ፈቃድ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸውም ይደነግጋል፡፡

ነገር ግን በግል በቤት ውስጥ ከሚተከሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሃይል መሙሊያ ማሽኖች ፈቃድ መጠየቅ የማይጠበቅባቸው መሆኑን ያመላከተው የተቋሙ መረጃ ከዚህ ውጭ ግን ማናቸውም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሃይል ሙሌት የሚሰጡ ማሽኖች መትከል የሚቻለው ከባለስልጣኑ ፈቃድ ሲያገኝ ብቻ መሆኑንም አመላክቷል።

መመሪያው ለህዝብ በሽያጭ የኤሌክትሪክ ሃይል ሙሊት አገልግሎት የሚሰጡ ታሪፋቸው በባለስልጣኑ ሲጸድቅላቸው ብቻ ተግባራዊ እንዲያደርጉም የሚስገድድ ነው።

ከኤሌክትሪክ ታሪፍ ጋር በተገናኘ ከባለስልጣኑ የሃይል አቅርቦትና ሽያጭ ፈቃድ የወሰዱ ተቋማት ለበለስልጣኑ የታሪፍ ፕሮፖዛላቸውን አቅርበው ሲያፀድቅ ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ መመሪያው ያሳያል፡፡

ለማሽኖቹ መትከያ ቦታዎችን በተመለከተ መመሪያው በየ50 ኪሎ ሜትር በየመንገዶቹ ግራና ቀኝ በኩል እንዲቋቋም መመሪያ የሚፈቅድ ሲሆን በተጨማሪም ለከባድ ተሸከርካሪዎች ማለትም አውቶቢስ እና የጭነት ተሸከርካሪዎች በየ120 ኪሎ ሜትር ቢያንሰ አንድ የሃይል መሙያ እንዲኖር ይፈቅዳል፡፡

ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ እገዳ ጣለች ሲሆን መኪና አስመጪዎች የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ላይ ናቸው፡፡

ይሁንና ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች የመለዋወጫ እጥረት፣ የጥገና ባለሙያ፣ ሀይል መሙያ ማዕከላት እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማት አልተሟሉም፡፡

በዓመት ለነዳጅ ግዢ ከአራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የምታደርገው ኢትዮጵያ ይህን ወጪ ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡

ለአብነትም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀድ፣ የነዳጅ ድጎማዎችን ቀስ በቀስ ማንሳት፣ አሮጌ እና ረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጡ መኪኖችን ማገድ እና ሌሎችም እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች፡፡

የፌደራል መንግስት የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ ለማስገባት እና የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል በሚል በነዳጅ ላይ ድጎማ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ ግን ይህን የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ እያነሳች ትገኛለች፡፡

አሁን ላይ አንድ ሊትር ቤንዚን 101 ብር ሲሸጥ ናፍጣ በ98 ብር እየተሸጠ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ዋጋ ቅናሽ በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *