ሲዳማ ክልል እንዲሆን ብዙ ዋጋ ብንከፍልም የጠበቅነውን ለውጥ ማየት አልቻልንም ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

የክልሉ መንግስት ግን በዓመት ከ60 ሺህ በላይ የስራ እድል እየፈጠርኩ ነው ሲል የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ክልል እንሁን ከሚል ወደ ልማት ጥያቄ ዞሯል ብለዋል

በቀድሞው የደቡብ ክልል ስር ከነበሩ ዞኖች መካከል አንዱ የነበረው የሲዳማ ዞን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 11ኛው የኢትዮጵያ ክልል ሆኖ ተዋቅሯል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በአራት ዞኖች እና አንድ ከተማ አስተዳድር የተዋቀረው ሲዳማ ክልል ከህዝበ ውሳኔ በኋላ ህይወት እንዴት እየቀጠለ እንደሆነ ኢትዮ ነጋሪ የክልሉን ነዋሪዎች አነጋግራለች፡፡

ለደህንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ እንዳለን ከሆነ “ሲዳማ ክልል እንዲሆን ቤተሰቤን ጨምሮ ብዙ ወጣቶች ዋጋ ከፍለናል፡፡ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው እየተጠቀሙ ያሉት፣ ስራ ማግኘት አልቻልንም” ሲል ተናግሯል፡፡

“ሲዳማ ክልል ሆነ ስንባል ብዙ ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ጥቂቶች ናቸው እየተጠቀሙበት ያሉት፡፡ በክልሉ እየተፈጠረ ያለው የስራ እድል እና የስራ ፈላጊ ሰዎች ቁጥር የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ከዩንቨርሲቲ ከተመረቅሁ አራት ዓመት ቢሆነኝም እስካሁን ስራ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ስራ ይዤ የራሴን ቤተሰብ የመመስረት እቅድ ቢኖረኝም ይህ እስካሁን አልሆነም” ሲል የነገረን ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የይርጋለም ከተማ ነዋሪ ነው፡፡

በሐዋሳ ከተማ መንደር 4 ነዋሪ መሆኗን እና በንግድ እንደምትተዳደር የነገረችን ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ በበኩሏ “ኑሮ ውድነት ሊገለን ነው፡፡ የቀድሞው ደቡብ ክልል በነበረበት ወቅት ስራ ብዙ ነበር፣ ሸማቹ ብዙ ነበር፡፡ አሁን ገበያ የለም፣ ሱቅ ከፍተን አፋችንን ከፍተን ነው የምንውለው፡፡ አየር የለም ልጆቼን ማኖር ከብዶኛል፡፡ በተለይ የቀድሞው የደቡብ ክልል ከተበተነ እና ሰራተኞች ከተማዋን ከለቀቁ በኋላ የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተዳክሟል” ብላለች፡፡

“የመንግስት ተቋማት አመራሮች ለኮሪደር ልማት እና ሌሎች ምክንያቶችን እየፈለጉ ገንዘብ አዋጡ እንባላለን፣ አገልግሎት ፈልገን ስንሄድ ደግሞ ሙስና እንድንከፍል እንገደዳለን“ ያለው ደግሞ ሌላኛው የሐዋሳ ከተማ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ነው፡፡

በተለይም የገቢዎች፣ ንግድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ነዋሪዎቹ የተናገሩ ሲሆን ነጋዴዎች በተጽዕኖ ምክንያት ንግዳቸውን እየዘጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ለማ ኦያቴ በበኩላቸው የሲዳማ ማህበረሰብ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ሲያነሳው የነበረው ጥያቄ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደ የህዝበ ውሳኔ ምላሽ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልልነት በማንም ችሮታ የተገኘ አይደለም የሚሉት አቶ ለማ የሲዳማ ልጆች በከፈሉት መስዋዕትነት የተሰጠ ነውም ብለዋል፡፡ ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ ብዙ ጥቅሞቹን እንዳጣ በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ይነገራል ይህ ግን ትክክል አይደለም ሲሉ አቶ ለማ ገልጸዋል፡፡

ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ ፓርቲያችን ሙስና የሚጠፋ፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ይኖራል፣ ለወጣቶችም የስራ እድል በስፋት ይፈጠራል ብሎ ጠብቆ ነበር የሚሉት አቶ ለማ እነዚህ እንዲፈቱ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግላችንን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡

“ብዙዎች አሁንም ሲዳማ በደቡብ ክልል ውስጥ ቢቆይ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ጥያቄው በሰላማዊ መልኩ መመለሱ ጥሩ ነው፡፡ አሁን ላይ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል የለም፣ የሙስና ችግር ይፈታል ብለን እንጠብቅ ነበር፡፡ የተሰሩ የልማት ስራዎች እንዳሉ እንገነዘባለን ነገር ግን ከህዝቡ ጥያቄ እና ከሚጠበቀው አንጻር ያልተሰራው ይበልጣል” ሲሉም አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡

ገዢው ፓርቲ የሰራነውን የልማት ስራ ጎብኙልን ነው የሚለን እንጂ ስራዎች ገና ከጅምሩ በእቅድ ደረጃ ላይ እያሉ አስተያየት እንዲሰጡ እንደማይጋብዛቸውም ገልጸዋል፡፡

ሲዳማ ክልል በሆነ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ የሰራተኞችን ደመወዝ ሳይቀር ለመክፈል ተቸግሮ እና ህዝቡ የጠበቀው እና የክልሉ አቅም አለመመጣጠን አጋጥሞ ነበር የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በለጠ ጽጊሞ ናቸው፡፡

ሰብሳቢው አክለውም ሲዳማ ክልል ሲሆን በሀብት እንደሚትረፈረፍ የሚያስቡ ሰዎች ነበሩ ፣ ችግሮች በነዋሪዎች ላይ ከጠበቁት በላይ ሲሆንባቸው ክልል በመሆናችን ምን አተረፍን እንዲሉ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ከዚህ በፊት ሲጠይቀው የነበረው ክልል እንሁን ነበር አሁን መሰረተ ልማት ይሟላልን፣ ስራ እድል ይፈጠርልን እና አገልግሎት አሰጣጡ ይዘምንልን ወደሚሉ ጥያቄዎች ተቀይሯልም ብለዋል አቶ በለጠ፡፡

የሲዳማ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ወሰንየለህ ሰምኦን በበኩላቸው በህዝበ ውሳኔ መሰረት ክልላዊ አስተዳድር ከተቋቋመ በኋላ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በተካሄዱ ውይይቶች መሰረትም የሕዝብ ጥያቄ ምንድን ነው የሚለውን ለማወቅ ተሞክሯል የሚሉት ሀላፊው ዋናው ጥያቄ የልማት ጥያቄ ሆኖ በመገኘቱ የክልሉ መንግስት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቷልም ብለዋል፡፡

ቱሪዝም፣ ግብርና፣ ማዕድናት እና ሌሎች ዋና ዋና ስራዎች ዙሪያ ሲዳማ ክልል ከክልሉ ህዝብ ባለፈ ወደ ማዕከላዊ ገበያዎች የሚልካቸው ምርቶች መጨመራቸውንም አቶ ወሰንየለህ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በዓመት ከ60 ሺህ በላይ ቋሚ የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል ያሉት ሀላፊው ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ የኢንቨስትመንት እና ሌሎች የልማት ስራዎችን እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ወሰንየለህ አክለውም ሲዳማ ክልል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በሰላም የሚኖሩበት ክልል መደረጉን፣ በህዝብ የሚነሱ ተጨማሪ የልማት እና የመልካም አስተዳድር ጥያቄዎችን እየፈታን እንሄዳለንም ብለዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *