ኢትዮጵያ ከውጪ ንግድ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፉት አራት ወራት ከወጪ ንግድ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡

በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ 480 ሺህ ቶን የተለያዩ ምርቶችን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደተገኘ ተገልጿል፡፡

የተገኘው ገቢ ካምናው ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር የ947 ሚሊየን ዶላር ብልጫ አሳይቷል ተብሏል፡፡

ከተገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ግብርና 53 ነጥብ 25 በመቶ ድርሻ ሲይዝ ማዕድን 37 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ 5 ነጥብ 43 በመቶ እንዲሁም ኤሌክትሪክና ሌሎች 4 ነጥብ 33 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡

ወርቅ፣ ቡና፣ ኤሌክትሪክ እና የጥራጥሬ ምርቶች በገቢም ሆነ በመጠን ከዕቅዳችው በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ምርቶች መሆናቸውን የሚስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከተላኩ ምርቶች መካከል 150 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ ተልኮ 674 ሚሊየን ዶላር ገቢ ሲገኝ 9 ቶን ወርቅ ኤክስፖርት በማድረግ 735 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱም ተገልጿል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አሳይቶ የነበረ ሲሆን የወርቅ ህገ ወጥ ንግድ፣ የጸጥታ እና ሌሎች ግብዓት እጥረት ለገቢው ጉድለት ዋነኛ ምክንያቶች ነበሩ፡፡

በተለይም በማዕድናት ህገ ወጥ ንግድ ላይ በተወሰዱ እርምጃዎች ከወርቅ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ቢያደርግም አሁንም የጸጥታ እና ህገወጥ ንገድ መስፋፋት ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ነው ተብሏል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔን ላይ የዋጋ ማስተካከያ ሊያደርጉ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ሸገር ሬዲዮ እንደዘገበው ከሆነ የንግድ ባንኮች በተበዳሪዎች ላይ ከ3 እስከ 5 በመቶ ጭማሪ ሊያደርጉ ነው ተብሏል፡፡

አሁን ለይ ባንኮች ብድር እስከ 17 በመቶ ወለድ በማስከፈል ለይ ሲሆኑ በቅርቡ በሚተገብሩት አዲስ የወለድ ማሻሻያ መሰረት ደግሞ ወደ 22 በመቶ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡

የባንኮች ብድር ወለድ ጭማሪ በተወሰነ ደረጃ ተረጋግቶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ሊያባብሰው እንደሚል የፋይናንስ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *