ውድድሩ የኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ትብብር፣ኢንፉሌንሰርስ እና ቬንደንስ የተሰኙ ተቋማት በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡
ሶስቱ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩት ተቋማት ከሁለት ወራት በፊት ወጣቶች በደን አጠባበቅ ዙሪያ በኢሴይ ራይቲንግ፣ ኢንፎ ግራፊ እና ቪዲዮ የታገዘ ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡
የኢንፉሌንሰርስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ናሆም ፈቃዱ እንዳሉት በተደረገው ማስታወቂያ መሰረት 80 ወጣቶች በውድድሩ ላይ እንደተሳተፉ ተናግረዋል፡፡
ከሁሉም ተወዳዳሪዎች ውስጥ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የወጡ ወጣት አሸናፊዎች ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር ሽልማት ተሸልመዋል፡፡

ወጣት ናሆም እንዳሉት ተቋማቸው ኢንፉሌንሰርስ ሁሉም ሰው ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ በሚል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
ለአካባቢ ጥበቃ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ለሚፈልጉ ሰዎች ነው የተቋቋመው፣የአየር ንብረት ለውጥ የባሰ ጉዳት የሚያደርሰው ወጣቶች ላይ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ ወጣቶች የተሻለ አስተዋጽኦ እና ጥረት እንዲያደርጉ በማገዝ ላይ ነን ሲሉም ወጣት ናሆም ተናግረዋል፡፡
ስለ አካባቢ ጥበቃ በኦንላየን እና በኦፍላየን ወጣቶች ባሉበት ቦታ ሁሉ እየሄድን ስለ አካባቢ ጥበቃ በትምህርት ቤቶች ሳይቀር እያስተማርን ነው የሚሉት ወጣት ናሆም ከግንዛቤ ፈጠራ ባለፈ ጥናቶችን እና አድቮኬሲዎች ላይ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢንፉሌንሰርስ ተቋም አዲስ አበባ ትኩረቱን ያደረገ ቢሆንም በቀጣይ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የመስራት እቅድ እንዳለውም ተገልጿል፡፡
የደን ጥበቃ ውድድር አሸናፊ ከሆኑ ወጣቶች መካከል አንዷ የሆነችው ጽዮን ጌቱ በበኩሏ “የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ፖለቲከኞችን እና የትልልቅ ሰዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ አካባቢ ጥበቃ የወጣቶችም ጉዳይ መሆን አለበት” ብላለች፡፡
ጽዮን አክላም ስለ አካባቢ ጥበቃ በኢንፎግራፊ ነበር የተወዳደርኩት፤ እኔ ከስድስት ወር በፊት በኮምፒውተር ሳይንስ በመጀመሪያ ድግሪ ነው የተመረኩት፡፡ ሽልማቱ አነስተኛ ቢሆንም ለእኔ ዋናው ነገር ገንዘቡ ሳይሆን እውቅናው መሆኑን ተናግራለች፡፡

ወደፊት እንደ አንድ የኢትዮጵያ ወጣት በቻልኩት አቅም ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር አለብኝ የምትለው ጽዮን አካባቢ ጥበቃ ላይ ባለመሰራቱ ምክንያት እንደ ወጣት ብዙ ነገሮችን አጥተናል ይህ መስተካከል አለበት ወጣቱም ለዚህ ማበርከት አለበት ብዬ አምናለሁ ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ትብብር ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ዮናስ ገብሩ በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራ የብዙ ተቋማት ቅንጅትን የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በተለይም በገጠር የሚኖረው ማህበረሰብ ህይወቱ ከደን ሀብት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዘላቂ የደን አጠቃቀም እና አጠባበቅ መሻሻል እንዳለበት አቶ ዮናስ ገልጸዋል፡፡
በጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 40 በመቶ ወደ 3 በመቶ ደርሶ ነበር፣ የደን ውድመቱ እጅግ አሳሳቢ ነበር ያሉት አቶ ዮናስ አሁን የደን ሽፋኑ ወደ 17 በመቶ ከፍ ማለቱንም አክለዋል፡፡
እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ ስለ ደን አጠባበቅ እና አጠቃቀም ያለው ግንዛቤ መስተካከል ያለበት ሲሆን ወጣቶችን ስለ አካባቢ ጥበቃ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዙ በሚል የሽልማት ፕሮግራም እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡
ሽልማቱ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ተካሂዶ 80 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል የተባለ ሲሆን በቀጣይ ወጣቶችን የበለጠ ስለ አካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚቀጥሉም ተገልጿል፡፡