በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በላይ ከልጅነቱ አንስቶ የአገራችንን ሙዚቃ በተለያዩ የአገራችን ቋንቋዎች በመዝፈን፣ የአገራችንን ሙዚቃ ከአገር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲደመጡ ያደረገው ጋሽ ማህሙድ አህመድ ማይኩን ሊሰቅል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ማህሙድ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የክቡር ዶክተር ማዕረግን መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፍ ዝነኛ የሆነውን የሙዚቃ አባት ከሙዚቃ አለም የመሰናበቻ ፕሮግራም በአዲ አበባ እና በአሜሪካ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል፡፡
የመሰናበቻ ሙዚቃ ፕሮግራም ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲ አበባ ሚለኒየም አዳራሽ የድምጻዊ ማሕሙድ አሕመድ የመጨረሻ የህይወት ዘመን ስንብት ደማቅ ኮንሰርት እንደሚዘጋጅ ተነግሯል ፡፡
በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይም የክቡር ዶ/ር አርቲስት ማሕሙድ አሕመድ የሙዚቃ ሕይወት ላይ የተዘጋጀ መፅሀፍ እንደሚመረቅም ተገልጿል፡፡
ድምጻዊ ማህሙድ የተወለደው ሚያዚያ 30, በ1933 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ መርካቶ በተለምዶ አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
ድምጻዊው በልጅነቱ ከሊስትሮ ሙያ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንዳደገ ማህመድ ባንድ ወቅት ለኢቲቪ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግሯል፡፡
የሙዚቃ ሕይወቱ ሀ ብሎ የተጀመረው አንድ ክለብ ውስጥ ሳንድዊች እንዲያቀርብ በተቀጠረበት ጊዜ ሲሆን እንደ አጋጣሚም ሆኖ በዚያው ክለብ ውስጥ ታዋቂው የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ ጥላሁን ገሠሠ ይዘፍንበት የነበረ ቦታ ነበር፡፡
በሙዚቃ ሕይወቱ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የሚናገረው ማህሙድ ዘመኑ ለሙዚቀኞችም ሆነ ለሙዚቃ ዕድገት የተመቻቸ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
እንደሚናገረው ከሆነ ይሔ ዕድገትም የተገኘውና እዚህ መድረስ የተቻለው በዱሮ ሙዚቀኞች መስዋዕትነት ነው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ያሳተመው የውጪ ሃገር አሳታሚ ክሬመርስ የተባለው የቤልጂየም ሬከርድ ሌብል የመሃሙድን 2 ዘፈኖች የያዘ ኤልፒ (LP) በ1976 አ.ም አሳትሟል፡፡
በወቅቱ ይህ ሬከርድ በጣም ጥሩ የሚዲያ ዳሰሳዎችንም አግኝቶ ነበር:: (ኒዮርክ ታይምስን ጨምሮ) የአለም ምርጥ 10 ወርልድ ሚውዚክ ቻርት ውስጥም ለመግባት ችሎ ነበር::