ኢህአፓ መንግስት በሚፈጽማቸው የድሮን ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎችን እየገደለ ነው ሲል ከሰሰ

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ “የዜጎችን ህይወት የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት መንግሥት ቢሆንም በሚያሰማራቸው የጸጥታ ሃይሎችና የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጭምር የዜጎች ህይወት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደቅጠል እያረገፈ ይገኛል” ብሏል፡፡

ኢሕአፓ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ህገመንግሥቱን የመንግሥት አካላት ራሳቸው ካላከበሩት እንዴት ሊያስከብሩት ይችላሉ “በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚደረጉት ግድያዎች ይቁሙ” ሲል አሳስቧል፡፡

እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከመዘገብ ቢቆጠቡም በውጪ የመገናኛ ብዙሀን ጭምር ጥቃቱ መፈጸሙን እየገለጹ መሆኑን እና ፓርቲውም አጣርቻለሁ ያለውን በየክልሉ የደረሱትን ጥቃቶች አስታውቋል፡፡

ፓርቲው አጣርቻለው ባለው መሰረት ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱ ጥቃቶች የሟቾችን ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን እና ጥቃት ከተፈጸመባቸው ውስጥም ነፍሰጡሮች፣ የጤና ባለሙያዎች እና በትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች እንደሚገኙበት አመላክቷል፡፡

በመሆኑም  “ወደፊት ትውልድ እንዲከፍል በብድር በመጣ የጦር መሳሪያ ንጹሀን ዜጎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄድ አግባብነት የለውም”፤ መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ለማለት እንደዚህ ያለውን ሁኔታ በዝምታ ማስቀጠል አይችልም ሲል ኮንኗል፡፡

ኢሕአፓ  መንግሥት በተለይ የጦርነት አውድማ በተደረጉት በአማራ፣በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝና በደቡብ ክልሎች ዉስጥ የሚደረገውን ህገመንግሥቱን እየጣሱ ያሉትን፣ መንግሥት መር የዜጎች ግድያዎችን በጥብቅ ማውገዙን እና  ጦርነቶቹ አሁኑኑ ይቁሙ ሲልም አሳስቧል፡፡

የፌደራል መንግስት ክልል የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም አደራጃለሁ በሚል ውሳኔ ካሳለፈበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች አማካኝነት ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባሳለፍነው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ በስልክ ተወያይተዋል የተባለ ሲሆን የአማራ ክልል ሰላም ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው አስታውቀው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣቸው ተከታታይ ሪፖርቶች በአማራ ክልል ንጹሃን ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ እና ምሁራንን ጨምሮ ሰዎች በጅምላ እየታሰሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ከሰኔ ወር ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ጦርነት ከ160 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

ግድያ ከተፈጸመባቸው ዜጎች መካከል የአዕምሮ ህመምተኞች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *