አዲሱ የኢትዮጵያ ሚዲያ ህግ ማሻሻያ ከሚዲያ እና ህግ ባለሙያዎች ማህበራት ተቃውሞ ገጠመው

የሚዲያ ህግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ሁሉን ያሳተፈ ውይይት በአስቸኳይ እንዲደረግበት  ተጠይቋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በስራ ላይ ያለው የሚዲያ ህግ እንዲሻሻል ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወሳል፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ በቂ የባለድርሻ አካላት ውይይት ሳይደረግበት ወደ ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ትክክል እንዳልሆነ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የጋዜጠኞች፣ ህግ እና ሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ማህበራት ተችተዋል፡፡

14 የጋዜጠኞች፣ ህግ እና ሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ማህበራት በጋራ ባወጡት መግለጫ የሚዲያ ህግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የሕዝብንም ሆነ የባለድርሻ አካላትን ድምፅ በተገቢ ያላካተተ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡

የጋዜጠኞች ማህበራት እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶቹ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013ን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴ መምራቱንም አስታውቀዋል፡፡

መግለጫው በአዋጁ ከለላ ተሰጥቷቸው የነበሩ የቁጥጥርና ሚዛን መጠበቂያዎች በረቂቅ አዋጁ ሊሻሩ የሚችሉ መሆናቸው በእጅጉ እንደሚያሳስባቸውም ተጠቅሷል፡፡

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የመገናኛ ብዙኃን ሕግ በርካታ አንቀፆች ይዘትና መንፈስን የሚቀይር  መሆኑን እና ረቂቅ ማሻሻያው የአካሄድና የይዘት ግድፈቶች በስፋት የሚስተዋሉበት  ነውም ተብሏል፡፡

በረቂቁ ማሻሻያ ላይ ምንም ዓይነት የሕዝብ ውይይቶች ባለመከናወናቸው የሲቪል ማኅበረሰቡን፣ የሚዲያ ሙያተኞችን እንዲሁም የሌሎች መብቶች ተሟጋቾችንና የማኅበረሰብ ድምፆች እንዳይሰሙ የሚያደርግ እንደሆነም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም ማሻሻያውን ለማዘጋጀት የተሔደበት መንገድ ግልጽነትና አሳታፊነት የጎደለው ነው የተባለ ሲሆን የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት በገለልተኛ አካል በተሠራ ጥናት ስለመለየቱ የቀረበ ማስረጃ  አልቀረበም ሲልም ተገልጿል፡፡

ጉዳዩ አስችኳይ መፍትሔም ሊፈለግለት እንደሚገባው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ አሳስበዋል፡፡

መግለጫውን ካወጡት መካከል የኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች ማህበር፣ የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል፣የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ እና ሌሎችም ናቸው፡፡

ዩኔስኮ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ፣ ከ1998 እስከ 2016 ዓ፣ም በነበሩት ዓመታት አፍሪካ ውስጥ ጋዜጠኞች የተገደሉባቸውና ፍትህ ካላገኙባቸው አገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስታውቋል፡፡

በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ሁለት ጋዜጠኞች እንደተገደሉ ዩኔስኮ ባለፈው ሳምንት በአዲ አበባ አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ውስጥ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ዓላማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከላካይ ቡድን (ሲፒጄ) በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ዙሪያ ከዚህ በፊት ባቀረበው ሪፖርት፣ ጋዜጠኞች የዘፈቀደ እስሮችና አካላዊ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙባቸውና ሕጋዊ ገደቦችም እንዳሉባቸው መግለጹ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *