የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ለጎረቤት አገራት ከሸጠው ኤሌክትሪክ ኃይል ከ31 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱን አስታወቀ።
ተቋሙ ለጅቡቲ ከሸጠው ከ169 ሺሕ 710 ሜጋ ዋት በላይ የሚኾን ኃይል፣ 10 ሚሊዮን 379 ዶላር እና ለኬንያ ከሸጠው ከ314 ሺሕ 931 ሜጋ ዋት በላይ የሚኾን ኃይል ከ20 ሚሊዮን 470 ሺሕ ዶላር ማግኘቱ ተገልጿል።
በተመሳሳይ፣ ተቋሙ ለሱዳን ካቀረበው ከ13 ሺሕ 185 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ከ659 ሺሕ በላይ ዶላር ያገኘ ሲኾን፣ በሱዳኑ ጦርነት ሳቢያ ተቋሙ በሩብ ዓመቱ ለአገሪቱ ለማቅረብ ካቀደው ኃይል ውስጥ ያቀረበው 15 በመቶውን ብቻ እንደኾነ ተገልጧል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በዲጂታል መረጃ ማቀነባበር ከተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች በሩብ ዓመቱ ውስጥ ከተሸጠው ኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ፣ ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል ተብሏል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካው ቢትኮይን ክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ በኢትዮጵያ መሰማራቱን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትኛውንም ክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት እንዳልፈቀደ እና ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ ሰዎችም በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቆ ነበር፡፡
ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ የቢትኮይን ግብይት መፈጸም የሚያስችሉ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርጉ ኩባያዎች ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት እንዲደረግ ያልፈቀደች ሲሆን የዳታ ማዕከል ግንባታዎች እንዲካሄዱ ግን ስምምነቶችን በመፈራረም ላይ ነች፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የዎልስትሪቱ ቢትፉፉ የተሰኘው የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ በኢትዮጵያ መሰማራት የሚያስችለውን ሂደት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ማካሄድ የሚያስችል የ80 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ሀይል መሰረት ልማት መግዛቱን ገልጿል፡፡
ቢትፉፉ የተሰኘው ይህ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኤሌክትሪክ ዋጋ ርካሽ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ከሰባት ወራት በፊት ዌስት ዳታ ማዕከል የተሰኘው ኩባንያ የ250 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር ተፈራርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የቢትኮይን ግብይት እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ እና ቻይና ክሪፕቶከረንሲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከላቸውን ለመክፈት ፍላጎታቸው ከፍተኛ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የአይሲቲ ፓርክ ውስጥ የዳታ ማዕከላትን ለመገንባት ስምምነቶችን እየተፈራረሙ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሀገሯ እንዲመጡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ሌሎች ተቋማት በኩል እያስተዋወቀች ትገኛለች።
በዚህም መሰረት እስካሁን 25 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር የሀይል አቅርቦት ስምምነትን ተፈራርመዋል ተብሏል።